ወንድም ጀማል፡ እንደምን ዋልክልኝ !
እንደ ቀልድ የጀመርናት ውይይት ጠንከር እያለች ሄደችና ዛሬ ላቀርብ ያቀድኩትን አንኳር ስራ ፈንግየ ለአንተ መልስ ለመስጠት መጠመዴ በመካከላችን የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ ካለኝ ቅን እሳቤ የተነሳ መሆኑን አስቀድሜ ልገልጽልህ እወዳለሁ፡፡ መልሴን አዘገጃጅቸ ከመልስህ ግርጌ ለመለጠፍ ስሞክር መልሴ ተንዛዛ መስለ በዚያ በቂ ቦታ ባለመኖሩ ውይይታችን ወደዚህኛው ሜዳ ላዞረው መገደዴን ከይቅርታ ጋር ላሳውቅህ እወዳልሁ ! መልሴን ልጀምር . . .
ነገሮች ምንም እንኳን እውነት ቢሆኑ የሚገለጹባቸው ጊዜ ልንመርጥላቸው ይገባል ያልከው እውነት አለው ፡፡ ለዚያም ነው ለዜጎች መብት ረገጣ ድምጻችን እናሰማ የምለው ! ለኔ ይህ ሰአት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እየጎረግፉ ባለበት ሁኔታ ለመብት ጥብቃው እየተሰራ ያለ ስራ በለመኖሩ መፍትሄ ይፈለግለት ለሚለው አቤቱታ ሰአቱ አይሁን ነው ብየ አምናለሁ ! ይህን ካልኩ ዘንዳ ያናሳናቸውን ሃሳቦች ለመለየት እንዲያመቸን ቀዳሚ ሃሳቦቹን በአርዕስትነት እያስቀደምኩ መልስ ለመስጠት ልሞክር፡፡
የኮንትራት ሰራተኞች ስቃይ መከራ . . .
በመሰረቱ በአረቡ አለም የምናየው የዜጎቻችን መብት ጥሰት የሚታየው ከሃገር ውስጥ ጀምሮ ከሃገር ውጭ ባሉ የመንግስት ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ስር ባለው ያልተማከለ አስተዳደር እንደሆነ ጥቂት ምሳሌዎችን ልጠቃቅስልህ እዎዳለሁ ፡፡ ከመሰረታዊ ምክንያቶችም መካከል ዋነኛው በሃገራት መካከል የሁለትዮሽ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ አረብ ሃገራት እንዲላኩ መደረጉን በቅርቡ በሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አማካኝነት የተደረገው ጥናት ያመላክታል፡፡ በቅርቡ ይፋ በሆነው በዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ በተደረገው ጥናት በዜጎች ላይ የሚደርሰው በየመብት ጥሰት ከሃገር ቤት እንደሚጀምር በጉልህ አሳይቷል፡፡ ጥናቱ በዝርዝር ባወጣው መረጃ ህጋዊ ፍቃድ ያላቸው ስራና ሰሪ ቀጣሪዎች ቃል በገቡት ውል መሰረት ስራቸውን አለመስራታቸው ፤የኢምግሬሽን መስሪያ ቤቶች እድሜያቸው አስራ ስድስት የማይደርሱ ወጣቶችን እድሜያቸውን እንዳሻቸው ቆልለው ፓስፖርት እያወጡ ሲሰደዱ ዝምታም መምረጣቸው ፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ዜጎች ስለሚሄዱበት ባህል ቋንቋና ማህበራዊ ህይዎትና ስለስራው ጸባይ በቂ መረጃ ሳይኖራቸው ወደ ስራ እንዲሰማሩ ማድረጋቸው በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ ዜጎች በዚህ ሁኔታ ወደ ማያውቁት ሃገር ደርሰው ችግር ሲገጥማቸው በየሃገራቱ የሚገኙ የኢንባሲና የቆንስል መስሪያ ቤቶች በቂ የሰው ሃይልና ዝግጅት የሌላቸው በመሆኑ በዜጎች የሚደርሰውን የመብት ረገጣ መከላከል አለመቻላቸው እንደ ዋንኛ ምክንያት መውሰድ እንችላለን፡፡ እኔም ይህም መስሉን መረጃ በተለያየ ጊዜ በማቀርባቸው ዘገባዎችና መጣጥፎች ማቅረቤን የምታውቅ ይመስለኛል፡፡ ይህም ችግር እንደ ሃይማኖቱ የመብት ጥያቄ ከመንግስት ጣት ስር ያለ ነው መከበር መጠበቅ ያለበት የዜጎች መብት ነው ! የችግሩንና ስፋት መጠን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከራሳቸው ከችግሩ ዳፋ ከተዳረጉ ወገኖቸ በግንባር አይቻለሁና ልናገረው ግድ ይለኛል. . .የዜጎች በህገ መንግስቱ የመጠበቅ መብታቸው ተሸራርፏል ፤ ተገፏል እያልኩህ ነው ! አትኩሮትና ልንሰጠው ይገባል እያልኩህ ነው ! ለሰብዕና ዋጋ እንስጥ እያልኩህ ነው ! በችግሮቻችን እኩል በህብረት ድምጻችን እናሰማ ነው የምልህ ! ከዚህ በላይ መሄድ አልፈልግም . . .የሙስሊማኑን ጉዳት በሚመለከት አልጀዚራን ጨምሮ በተለያዩ የአረብ መገናኛ ብዙሃን የተሰራጨውን ውይይት. . .
በተረፈ በአልጀዚራና ከሰላሳ አራት በላይ የአረብ መገናኛ ብዙሃን የተሰራጨውን ውይይት በጽሞናና በአጽንኦት ተከታትየዋለሁ ! አዝኛለሁ ! ያዘንኩትም የሃገራችን መንግስት በቀላሉን የጣልቃ ገብነቱን ጥያቄ መልሶ ጉዳዩን ማብረድ ሲገባ ጉዳዩ እዚህ ደረጃ መድረሱና ዳግም በአረቦች አፍ ስላስገባን ነው ያዘንኩት ! ይህም ችግር የቤት ሰራተኞች ከመቅጠር ጀምሮ በሃገር ቤት በኢንቨስትመንቱ ከፍተኛ ተሳትፎ በማህበራዊ ህይዎቱ እየተዋሃዱን ያሉትን አረቦች የሚያሸሽ ሁኔታ
እንዳይፈጥር ስጋት አለኝ፡፡ አጠቃላይ ሂደቱ "ገጽታችን እንቀይር" እየተባለ የሚወተወትለትን የመልካም ገጽታ ግንባታ በሚንድ መልኩ መቅረቡ እንደ ኢትዮጵያዊ ይጎዳናል እልሃለሁ፡፡ እዚህ ላይ ሳልቅስልህ የማላልፈ ነገር ቢኖር አረቦቹ ሙስሊም አባቶች በማያገባቸው የገቡበትን አካሄድ አልወደድኩትም፡፡ አስተያየታቸው የግል በመሆኑ ባልቃዎማቸውም ዘመናትን ተሻግረውና ሩቅ ሄደው የዶም ክርስቶፋኦ ደ ጋማን ታሪክ በራሳቸው ትርጉም አንጻር እያወሱ የነካኩበት ሁኔታ የሚለያየን የታሪክ ትንኮሳ ነውና አልተመቸኝም፡፡ የኛ ጉዳይ መፈታት ያለበት በራሳችን ነው ! እዚህ ላይ ሳልገልጸው የማላልፈው የውይይቱ ተካፋይ የነበሩት ኢትዮጵያዊው የሃይማኖት አባት ሸህ ጃበር አደም የሰጡት አስተያየትና መግለጫ በተገቢው ቦታ ሳይናዛዛ የቀረበ በመሆኑ ወድጀዋለሁ፡፡ ሽህ ጃብርን ከውይይቱ በኋላ አግኝቻቸው ብዙ አውግተናል፡፡ ጥያቄያቸውን በተዋረድ ለመንግስት ተወካዮች አሰምተው ሰሚ ባለማግኘታቸው በሃገር ውስጥ ያሉ ሙስሊማን ድምጻቸው ይከበር ዘንድ ድምጻቸው ለማሰማት መገደዳቸው ይህ አባት ገልጸውልኛል ፡፡ በቀጣይ ልንወያይም ቀጠሮ ይዘናል፡፡ በተረፈ የኔ የበፊትም ሆነ የአሁን አቋም ሸህ ጃበር አደም የጠየቁት "መንግስት በህገ መንግስቱ የደነገገውን የእምነት ነጻነት አይጣስ ፤በሃይማኖት ጣልቃ አይግባ!" የሚለውን ጥያቄ እደግፋለሁ፡፡ ይህም በመሆኑ መሆኑ በሃገር ቤት ድምጻቸው ይሰማ የሚለውን የመብት ጥያቄ ያቀረቡትን ወገኖች ጥያቄ ነፍሴ ፈቅዶት አቀንቅኛለሁ ! ይህ አቋሜ በአሁኑ ሰአት ተቃውሞም ድጋፍም እያጎረፈልኝ ያለ አደገኛ አቋም ቢሆንም የፈቀድኩትን በመሆኑ ሁሉንም በጸጋ የመቀበሉን ልምድ ረድቶኛል፡፡ የማደርገው የሌላውን መብት መጋፋት የማትሻው የነፍሴን ይሁንታ አዳምጨ እንጅ በአድርባይነት የሚደለል ተፈጥሮ የሌኝ በመሆኔና፤ በማንም ድለላ ይሁንታ የማልሰጥ ላመንኩብትር ግንባሬን የሚያሰጥ ውሳኔው ደፍሬ የምትቀበል ነፍስ ባለቤት በመሆኔ አያስጨንቀኝም !
"አቅጣጫ ማስቀየር እንዳይመስልብህ" ላልከው . . .
በአልጀዚራ የተላለፈውን ውይይት ተከትሎ ብዙ ጽሁፎችን ከኔ ሲጠበቅ እንደነበር ገልጸህ ያም ሆኖ ወደ ዜጎች መብት ጥበቃ ጉዳይ መሻገሬ "የትኩረት አቅጣጫ " ለማስቀየር እንዳይመስልብኝ መስጋትህን በገደምዳሜ ነግረህኛል፡፡ እመነኝ ! የትኩረት አቅጣጫ የማስቀየር ሃሳብ የለኝም ! የዜጎች ጉዳይ ዛሬ ያነሳሁት አዲስ ነገር አይደለም ፤ ሁሌም መፍትሄ እንዲያገኝ የማቀነቅንለት ዋንኛ ጉዳይ በመሆኑ እንጅ የሙስሊማኑን የመብት ጥያቄ አጀንዳ ለማደባበስ አለመሆኑን ሁሉም የጠረጠሩኝ ሃሳቤን ቢረዱ ደስ ይለኛል ! በግድ ተረዱልኝ ግን አልልም ! ለስራ የሚመጡ ዜጎችን መብት መከበር ዙሪያ ለማደርገውን ትግል መራጃ ካስፈለገ የፌስ ቡክ ገጼን እንኳ ወደ ኋላ ሄደህ መመልከት ትችላለህ፡፡ እመነኝ ! አቅጣጫ የማስቀየር እርኩስ መንፈስ አልተጠናዎተኝም ! እንኳንስ የሙስሊም ወገኖቸን ጥያቄ አቅጣጫ ላስቀየርና ላድበሰብሰው ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ድምጻቸው እንዲሰማ ሌት ተቀን ጥረት ማድረጌን ባሳለፍናቸው ጥቂት ሳምታት ብቻ የሰራኋቸውን ዘገባዎችና መጣጥፎች እማኝ ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ በጅዳ በሪያድና በግብጽ የተከናዎኑትን ጠንካራ ተቃውሞዎችን ያለመታከት ሽፋን የሰጠሁበት ዋናው ምክንያት በሙስሊማኑ ጥያቄ ዙሪያ እምነት ስላለኝ እንጅ ማንም አስገድዶኝ አለመሆኑን ትረዳው ይሆን ? እናም አቅጣጫን የማስቀየር አላማውም ፍላጎቱም የለኝም ! አዲዮስ ! የመካው ጸሎትና ሙስሊም "ወዳጆችህን አስከፋ""ያልከው የኔ መረጃ . . .
"በብዙ ሙስሊሞች መንፈስ ታላቅ የሞራል ተሀድሶን ፈጥሮ የነበረውን የታላቊ ሀረም (መካ) ኢማም ሽህ አብዱረህማን ሱዴስ ኢትዮጵያውያንን ያጣቀሰ ዱዐ በተመልከተ ያሰፈርከው ጽሁፍ ብዙ ወዳጆችህን ደስ እንዳላሰኘ አስተውለሀል? " ላልከው የኔ ምላሽ . . .በመካ ሰንሰለታማ ተራሮች ስር በሚገኘው በታላቁ ሃራም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተጠቅሶ ጸሎት ተደረገ ተባለ፡፡ ወሬው እንደጉድ ተናኘ ! እኔም እንደለመድኩት በጸሎቱ ዙሪያ መረጃ ለማቀበል መረጃ ሳሰባስብ ያላሰብኩት መረጃ ገጠመነኝ ፡፡ የመካ ኢማም በሆኑት በድመጸ መረዋው በታዋቂው አሰጋጅ በሸህ አብድረህማን ሱዴስ ጸሎት ተደረገ ቢባልም በተባለው ቀን በጸሎቱ የኢትዮጵያ ስም አለመነሳቱ በማረጋገጥ መረጃው የተሳሳተ መሆኑን በፊት ገጼ ማስተባበሌ ወንጀል አይመስለኝም፡፡ ከውሸት እውነት ማውራቱ ይቀለል ማለቴ ካስቀየመ ችግር የለብኝም፡፡ ወዳጀ ጀመል እውነቱን ልንገርህ መቸም ዋሽቸ ወዳጆቸን ከማስደሰት ወዳጆቸ ቢርቁኝ ይቀለኛል ብልህ ግራ አትጋባ ! ከዚህ በተረፈ ይህንን ተንተርሰህ በሰጠህው አስተያያት ካንተ የማይጠበቅ ሚዛናዊ ያልሆነ ከውርፋ ያልተናነሰ በመሆኑ ተከፍቻለሁ ! ሌላው በሰጠህው አስተያየት "በሌላው ሃይማኖት ጣልቃ ገብቶ የሚሰራ ስህተት" አደጋው እጥፍ እንደሆነ አድርገህ ማቅረብህ ግን እጅጉን ጎድቶኛል ! በሃይማኖት ጉዳይ እንደ ቀሩት ማህበራዊን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ገብቸ መፈትፈት ቀርቶ መነካካቱን እንደማልወደው አንተም የምታጣው አይመስለኝም !
በያዝኩት የድጋፍ አቋም የሚስተዋለው ድጋፍና ተቃውሞ. . .
ወንድሜ ጀማል መሃመድ ፡ ዛሬ ካንተ ጋር የሚያነጋግረንን ጨምሮ ባሳለፍናቸው ጥቂት ሳምንታት ብቻ ያጋጠመኝን በርካታ ድጋፍ ጨምሮ ጠንከር ጠንከር ያሉ ተቃውሞዎችም ገጥመውኛል፡፡ ድካሜን ቆጥረው በሰራሁት ስራ የተደሰቱት ለላኩልኝን የምስጋና መልዕክት ምስጋናየ ይድረሳቸው ከማለት ባላፈ ሌላ መጨመር አልሻም፡፡ በአንጻሩ በርካታ በሙስሊም ወገኖቸ ባቀረብኩት ዘገባና ጽሁፍ የተቃዎሙት ከፖለቲካና ከሃይማኖቱ ጋር እያጋጩ ያላሉኝ የለም፡፡ ያየሁ የሰማሁትን የሙስሊማን ወገኖቸን የመብታችን ይጠበቅ የተቃውሞ ድምጽ በማሰማቴ "የተደበቀውን የጽንፈኞች አቋም ታንጸባርቃለህ!" በማለት ድብቅ አላማ እንዳለኝ የገለጹልን ወንድሞች ያደረሱኝ የወቀሳ የውግዘት መአት ከበድ ይላል ፡፡ መሰረታዊው "መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይግባ!" የሚለውን መሰረታዊ የሙስሊማን ጥያቄ ያልገባቸው አንዳንድ ክርስትያን ወገኖቸም ቢሆን ከጥቂቶች በስተቀር ብዙዎች በስራየ አልተደሰቱም፡፡ ሃገር ቤት "የአወሊያ ኮሚቴ ተብየወች እንቅስቃሴ አገር የማፈረስ የሽብርተኛነት ተልዕኮ ነው" የሚለውን የመንግስትን ፕሮፓጋንዳ የሰሙት ክርስትያንና ሙስሊም ወገኖቸ ለዚህ ቡድን ደጋፊዎች በድምጽ ድጋፍ ከመስጠት እንድታቀብ የመከሩኝ ወገኖቸ የትየለሌ ናቸው ፡፡ ያም ሆኖ ሁሉም አልገባቸውምና እንዲገባቸው ከማድረግ ባለፈ ከአቋሜ ዝንፍ አልልም ! ወንድሜ ይህን ሁሉ መዘክዘኬ የምወደው ሙያና እውነተን መከተል ምን ያህል አደጋ እንዳለው ትረዳልኝ ዘንድ ግንዛቤ ይሰጥሃል የሚል እምነት ስላለኝ ብቻ ነው ፡፡ ይህን ከባድ ፈተና እኔ በተቀመጥኩበት ወንበር ተቀምጠህ ሙቀት ፍዳውን ተረዳው ባልልህም ጉዳዩን በተለያየ አቅጣጫ ትመለከተው ዘንድ አደራየ የጸና ነው !
ይህ በምንኖርበት በሳውዲ አረቢያ ዙሪያ ገብ የእስልምና ሓማኖቱ እውቀትና የተባ ብዕር ያላችሁ አንተና አንተን መሰል ወንድሞቸ ያንቀላፋ የተኛ አንበሳ መሆናችሁ ሲያስጨንቀኝ መክረሙን የምትዘነጋው አይመስለኝም፡፡ በአደባባይና በግልጭ ብዕራችሁን አንስታችሁ ሃሳባችሁን ማካፈልና የወገኖቻችሁን ድምጽ እንድታሰሙ ድሮ ሳይሆን ትናንት መጎትጎቴንም አለመሳካቱን ታውቀዋለህ፡፡ እናንተ በዚህ መንገድ እያላችሁ እኔና ጥቂት ወንድሞቸ በግል የሙስሊም ወገኖቸን ህመም እያመመን ፤ ህገ መንግስታዊ መብታችን ተነካ ብለው የሚያሰሙትን የወገኖቻችን ጩኽት ሰምተን ጩኸት ቅያሞታቸውን ለቀረው አለም እንዲሰማ ማድረጋችን ደግመህ ደጋግመህ አጢነው ! እናም በእስካሁኑ ሂደት ችግር ፈተንውን ገፍቸ እኔ የሚቻለኝን ሰርቻለሁ የሚል እምነት አለኝ ! ይህ ደግሞ በግል ሁሌም የመንፈስ እርካታ ከሚሰጡኝ ኩነቶች ወስጥ ቀዳሚው ነው ብልህ ማጋነን አይሆንብኝም !
አክባሪ ወንድምህ ነቢዩ ሲራክ !

No comments:
Post a Comment