

በሃገር ቤት የሙስሊም ተወካዮች ላይ የተወሰደውንና እየተወሰደ ያለውን
እርምጃ አጥብቀው እንደሚቃዎሙ በተለያዩ አጋጣሚዎች የገለጹልኝ በሳውዲ
አረቢያ ጣይፍና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሉሞች "ሸክዋ
አል አላህ !" ወይም "አቤቱታችን ለፈጣሪ እናሰማ!" በሚል ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት መካ ሃራም በሁለት
አውቶብስ መግባታቸውን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ከጥቂት ሰአታት በፊት በድቅድቁ ሌሊት ጉዟቸውን በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ወደሚገኘው
ታላቁ የመካ ካእባ መስጊድ ሲያደርጉ በመፈክር ደምቆ የነበረውን
የጸሎት ጉዞ በስልክ ተከታትየዋለሁ፡፡ ቁጥራቸው ከመቶ ሃምሳ በላይ የሆኑት እኒሁ ኢትዮጱያውያን ሙስሊሞች ከጥቂት ደቂቃዎች
በፊት መካ የገቡ ሲሆን በአይነቱ አዲስ ስለሆነ ይህን መሰል አቤቱታ አቀራረብ ምን እንዳነሳሳቸው የጉዞውን አስተባባሪዎችና አንዳንድ
የጉዞውን ተካፋዮች በስልክ አነጋግሬያቸው ነበር፡፡ ማንም ሳያደራጃቸው ሁሉም በያሉበት በመጠራራት እንደተሰባሰቡ የገለጹልኝ
አንድ የጸሎቱ አስተባባሪ ሲያስረዱ "ህገ መንግስቱ ይከበርልን ባሉ እንግልት የደረሰባቸውን ኮሚቲዎችና የተነሱበትን
አላማ እንደግፋለን. . .ለመንግስት ሃላፊዎች ተቃውሞና አቤቱታቸውን ለመስማት መክረን ባይሳካና እነሱም ድምጻችን ለመስማት
እንኳ ፈቃደኛ ባይሆኑም ምህረት ለማያጎለው አምላክ አቤቱታችን እናቀርባለን " በሚል "ሸክዋ አል አላህ
!" የሚል የህብረት ድምጻቸውን ለፈጣሪ ለማሰማት
መሰባሰባቸውን ገልጸውልኛል፡፡ እኒሁ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አረንጓዴ ቢጫና ቀይ የኢትዮያን ባንዴራ በመያዝና የኦምራን ነጭ
የጸሎት ልብስ "ኢህራማቸውን" አገልድመው ከእስልምናዋ መፍለቂያ እምብርት መካ ካእባ የደረሱ ሲሆን የፈጅር "የማለዳ" ጸሎታቸውን
በህብረት በማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸውልኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በታይፍ የሚገኙ ክርስትያን ኢትዮጵያውያን
በበኩላቸው ምንም እንኳን መካ ለመግባት ሃይማኖታቸው ባይፈቅድም የሙስሊም ወንድሞቻቸው በሃይማኖት ጣልቃ አይገባብን በሚል
ያቀረቡትን ህገ መንግስታዊ ጥያቄ እንደሚደግፉ ስልክ በመደወል ገልጸውልኛል፡፡ የዝርዝር ሂደቱን ተጨማሪ
መረጃዎች አቅም በፈቀደ መጠን አሰባስቤ ለማቅረብ እሞክራለሁ !
No comments:
Post a Comment