በረመዳን ዋዜማ
ከአምስቱ የእስልምና ሃይማኖት ቀኖናዎች መካከል የረመዳን ጾም በዋናነት
ይጠቀሳል፡፡ ረጅም በምለው የሳውዲ ቆይታየ ከ15 ያላነሱ የኢድ አልፈጥር በአላትን ከሙስሊም ወገኖቸ ጋር በመሆን አክብሬዋለሁ፡፡
እናም ያለፈውን እያወሳሁ ስለማዘክረውና ዛሬን የማለዳ ወግ ማስታዎሻየን
ስላደረግኩት የኢድ አልፈጥር ክብረ በአል በርካታ የማይረሱ የግል ትዝታዎችን የቋጠርኩበት ታላቅ በአል ነው፡፡ ረመዳን ጾም ከመጀመሩ
አስቀድሞ ቤት ከማጽዳት ፤ ከቤት ቁሳቁስ እስከ መባልዕት አቅርቦት ሁሉም እንደ አቅሙ ለማድረግ በዋዜማው የሚደረገው ዝግጅት ጥድፊያና
ውክበት ባይለየውና ቢያደክምም ያስደስታል፡፡ ከትንሹ የጾም ዝግጂት ከተምር ፍሬ ምርጫውና ጾም ማፍጠሪያ (ጾም መፍቻ) የሚሆነውን
እንደ አቅሙ ለመሸማመት ከሚደረገውን ዝግጅት አንስቶ በጾሙ ራስን ለማጽዳት በርካታ ነፍስ የፈቀዳቸው ስራዎችን ሲከዎኑ የሚስተዋለው
በረመዳን ዋዜማ ነው፡፡ የተጣላ (አፉ) ይቅርታ የሚባባልበት ፤ የሰውን ብድር የወሰደ ብድሩን የሚመልስበት አለያም ለወስደው ብርድ
(አፉ በለኝ) ብሎ የአበዳሪን የይቅርታ ይሁንታ አግኝቶ ወደ ነፍሱ የሚመለስበት ወቅት የሚጀመረው በዚሁ ወቅት ነው ! የአንዲት አረብና
የሃበሻዋ የቤት ሰራተኛ የረመዳን ዋዜማ ክስተት አይዘነጋኝም፡፡ በአንድ አጋጣሚ በሰራተኛዋ ላይ በደል አድርሳ ከስራ ያባረረቻት
ይህች አረብ አሰሪ እመቤት በረመዳን ዋዜማ ራሷን መላልሳ ስትጠይቅ ቅር ነፍሷን የሚጎዳ ነገር መስራቷ ተሰማት፡፡ ጸጽቷት አስታውሳ
ሰራተኛ ያገናኛትን ወንድም አፈላልጋ በማግኘት የበደለቻትን እህት ይቅርታ ጠይቃ የቀረ ደመወዟን እንደሰጠቻት ከስምንትና ዘጠኝ አመት
በፊት በገሃድ ያየሁትን ምስክር ነበርኩን ልናገረው ግድ ብሎኛል ! በተለያየ የስራ አጋጣሚ
የሚገናኙ፤ በጉርብትና አብረው የሚኖሩ፤ ትልቅ አይል ትንሽ አሰሪና ሰራተኛ ፤ ሁሉም በነፍሳቸው የሚገመግሙበት ፈታኝ ወቅት ቢኖር
የረመዳን ዋዜማ ነውና የወሩ ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚጀመረው ከዋዜማው እንደሆነ የረመዳን ጾም በመጣ በሄደ ቁጥር የምታዘበው እውነተኛ
እንቅስቃሴ ሆኗል ! በሁሉም ዜጎች ዘንድ ቸርነት ይስተዋላል! ሁሉም በየፈርጁ በአመቱ እንቅስቃሴያቸው አንዱ አንዳቸውን አስቀይመው
እነደሆነና እንዳልሆነ ፤ ያንዱን ሃቅ አንዱ ወስዶ ስህተት ፈጽሞ እንደሆነ ራሱን የሚፈትሸው በረመዳን ዋዜማ ነው ! የረመዳንን ዋዜማ በያዝነው አመት ያከበርኩት ከጅዳ 200 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኘው በነፋሻማዋና ተራራማ የጣይፍ ከተማ ነበር፡፡ እዚያው ከተማ ልጆቸን ይዥ በድካም የዋተተ ነፍሴን ላነቃቃት ዘናም ላድርግ ብየ እንዳቀና ምክንያት ከሆነኝ በፊስ ቡክ የማውቀው ወዳጀ ጋር በዋዜማው ባደረግነው ቆይታ በታዋቂው የዓዕምሮ በሽተኞች ህክምና መስጫ ያሉትን በርካታ ሃበሾች የሚረዱበትን መንገድ እኔም ተግቸ እንዳፈላልግ ተማጽኖኛል፡፡ የበርካቶች ወንድም እህቶቻችን ረገብ ያላለ በስደት የሚገጥም አደጋ እንታደገው ዘንድ በጸና ታሞ ጠያቂ ያጣውን የአሳዛኙን እረኛ ወንድም ታሪክ እያጫዎተ ይህንኑ ወንድምና የቀሩትን ህሙማን ሄደን እንድንጎበኛቸው አማክሮኛል፡፡ ከማማከርም አልፎ ተባብረን እንድንደግፋቸው ያጫዎተኝና ከፊቱ ያነበብኩትና ያየሁት ቅንነት የተሞላበት እንቅቃሴ ፈጽሞ አይዘነጋኝም፡፡ የረመዳን የጾምና የጸሎት ወር ከዋዜማው ጀመሮ ሲታሰብ ከይቅርታ ጀምሮ ደግ ደጉን በመተሳሰብ የታመመን መጠየቅ የከፋውን ማጽናናት የዋዜማዎችን ጉልህ መገለጫዎች መሆናቸው ለማስቃኘት በስሱ ያደረግኩት ሙከራ ተሳክቶ ከሆነ መልካም ነው !
ጾም ጸሎቱና ስጋቱ . . .
ድምጻችን ይሰማ !
ረመዳን ወር
በሰላም ቢጀመረም አሁንም በሃገር ቤት የሙስሊማን መብት አቅራቢዎች እየታሰሱ ዘብጥያ የመውረድ ዜና ከጸሎት ስግደቱ ሶም መፍታቱ
በፊት በየማህበራዊ መገናኛው ገጽ ሲናኝ ደግሞ የብዙ ወገኖችን አንድገት አስደፋ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከቀኑ ሃሩር ጸሃይ ጋር ጾሙ
ያንገላታቸው ሳይቀሩ ጾማቸውን ፈትተው (አፍጥረው) እንደወትሮው ዘና ከሚያደርጋቸው የአረቡ አለም ልዩ የረመዳን የቴሌቪዥን ድራማ ቀልድና የተለያዩ ቀልብ ሳቢ ዝግጅቶችን ብዙም አይታደሙም፡፡ ከዚህ ይልቅ በፊስ ቡክ Facebook ላይ አፍጥጠው የሚከታተሉት ማን ታሰረ ? ማን ተደበደበ ? ማን ህገር
ለቀቀ ? ምን ተፈጠረ ? ! አሜሪካ ራዲዮና ጀርመን ራዲዮ ምን አሉ ? በማለት ነጻ በሚባሉት መገናኛ ብዙሃን የህዝብ ልጆች በኮሚቴዎችና በተቃውሞው
ዙሪያ እየሆነ ያለውን መከታተል የአብዛኛው ሙስሊም እንቅስቃሴ ሆነ ፡፡ ረመዳን በተጀመረ በጥቂት ቀናት ልዩነት የሎንደን ኦሎምፒክ
የአለምን ቀልብ ስቦ ባለበት ወቅት እንኳ የአብዛኛው ሙስሊም ከዚህ ቀደም በንቃት የሚከታተለውን በየአራት አመቱ የሚመጣ የስፖርት
ድግስ ከቁብ ሳይሉት ያስተዋልኩብት ጊዜ ያሳለፍነው የረመዳን ጾም ወቅት ነበር ማለት የሚያስችሉ መረጃዎች አሉኝ ! እንደኔ እንደኔ
ፍጹም በቀላል መንገድ ሊፈታ የሚቸለው የሙስሊማንን ወገኖች ጥያቄ እንዲጦዝ መደረጉ ያሳዝናል ! በአልጀዚራ የአረብኛ ቴሌቪዥን በቀረበ
ሰፊ ውይይት በአረቦች እየተለወጠ መጥቶ የነበረው ገጽታችን ዳግም ሊጎድፍ ግድ ብሏል ፡፡ ከቅርብ አመታት ወዲህ ወደ ሃገራችን በመጉረፍ ላይ ያሉ ቱሪስቶች በአጭር ጊዜ
ውስጥ ቁጥራቸው በአስገራሚ ሁኔታ ወርዷል ! አረቦች ሲቀሩ በኮንትራት ስራ ወደ ሳውዲ እየመጡ ያሉ ወገኖች ቁጥርና የምናየውን ፍጹም
አሳዛኝ የወገን በደል ደግሞ ተበራክቷል፡፡ ረመዳን በገባ መባቻ እጅና እግሯን ተጠፍራ ታስራ የነበረች እህት አንዲት እህት በጅዳ
ቆንስል መስሪያ ቤት ቅጽር ግቢ በደረቁ ሌሊት ከውሃው ጉድጓድ ገብታ ተገኝታለች፡፡ ""የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት
ይቁም" በሚለው ወገን ግን ይህንንና ይህን መሰሉን በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ መስማት የሚችልበት አቅል ያለው አይመስልም፡፡ ተባብሮ ሰቆቃው
"ይቁም!" ለማለት ቀርቶ እየተበራከቱ በመጡት ደላሎች እየተፈጸመበት ያለውን ግፍ ለማስቆም ድምጻችን በአንድ ላይ
እናሰማ እንዳይባል በሰሞነኛውን መብት ጥየቃ በአይንና በጀሮው ላይ ግርዶሽ ጥሎበታል፡፡ የሙስሊማን መብት ይከበር ከማለቱ ጎን ለጎን "ሰብዕና ተገሰሰ ብለን ድምጻችን እናሰማ!" ማለት በጥቂቶች እይታ በሙስሊማን የሚቀርበውን የሃይማኖቱን ጥያቄ ማድበስበሻ እንደሆነ ተደርጎ የተቆጠረው በዚሁ በረመዳን ወቅት ነበር፡፡
መሰረታዊ የሁሉም ዜጎች ጥያቄ ነው
የሚለውን እንኳ ለመረዳዳት ፋታ አልተገኘም፡፡ መንግስትና መጅሊስ በሰፊው የሚሰራጨን መገናኛ ብዙሃን በመጠቀም
በመብት ጠያቂዎችና በኮሚቴዎች ዙሪያ ተቃውሞ ሲያደራጁና ሲያስተባብሩ ከረሙ ! በአንጻሩ በአዎሊያ እርምጃ ሲዎሰድ
በረመዳን መጀመሪያ ወደ ከተማይቱ እምብርት ወደ አንዋር መስጊድ የተሸጋገረው
ተቃውሞ አስገራሚ ትዕይንት ረመዳን አንድ ሲል ተጀመረ ! በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ሙስሊማን ሴት ሳይል ወንድ ፤ ህጻን ሳይል አሮጊት
በቀጣይ የአርብ አርቡ የህብረት ጸሎት አንዴ በዝምታ አፍን በመለጎም ፤ አንዴ በጭብጨባ ፤ አንዴ በካቴና የታሰሩ በመምሰል ፤ አንዴ
ነጭ ወረቀት ጨርቅና ሶፍት በማውለብለብ ጸጥና ረጭ እያሉ ያልታየ ያልተሰማ ሰላማዊ ተቃሟቸውን አሰሙ፡፡ በታህሪር አደባባይ የለውጥ
መንፈስ ተነቃቅተው ፤ ጠጠር ሳይወረውሩ የማህተመ ጋንዲን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በመከተል መብታቸውን የሚያስከብሩት ሙስሊማን መብትን
በሰላማዊ መንገድ ማስከበር እንደሚቻል ጥሩ ምሳሌዎች ሆነው ያሳዩት ከረመዳን ዋዜማ ጀምሮ ቢሆንም በረመዳን የታረው እጹብና ድንቅ
የሚባል ስነ ምግባርን የተከተለ ነበር ማለት ይቻለኛል …! በአንድ አርብ ሁከት ተነስቶ
አሸባሪዎች አውቶቡስ ሰበሩ ተባለ፡፡ ዳሩ ግና መሽቶ እየነጋ አርብ ደርሶ በጸሎት ሰአት ሰው በሚጎርፍበት የአንዋር መስጊድ ዙሪያ
ገብ "አሸባሪ" የተባሉት እንዲሰባብሩዋቸው ነው መሰል የከተማ አውቶቡሶች ከጸሎተኛው እኩል የመርካቶ ረድፈኛ
ሆኑ፡፡ ጸሎተኞች ግን " እንኳንስ አውቶቡስ ልንሰብር ጸሎት በመሆኑ ደከምን እንጂ ለመንግስታችን አጥበን በሰጠን . .
." እንዳሉ አንድ ወዳጀ ያጫዎተኝ በእርግጥም ፈገግ ያሰኛል፡፡
አዎ እዚህ ጂዳ አካባቢ የረመዳን ጾም ሲጀመር የተቃውሞ ድምጽ አሰምተው
ኮሚቴ የተዋቀረ ቢሆንም ኮሚቴው በመንግስት ተጽዕኖ ድብዛው መጥፋቱ ተነግሮምኛል፡፡ ሃላፊነቱን ሲረከቡ ምለው ተገዝተው ሃላፊነቱ
የተቀበሉት የኮሚቴው አባላትና አስተባባሪዎች የፍርሃት ሽሽት መምረጣቸውን ባላውቅም በማስፈራሪያው " ፈራን!" ቢሉም
ነፍሳቸው ያን ያህል አምናለችና ላያስገርም ይችላል፡፡ ያልተጠበቀውና የሚያስገርመው ሃገር ቤት እየሆነ ያለው ያስጨነቃቸው ያሳሰባቸው
በጣይፍና በአካባቢው ያሉ ወንድሞች በራስ ተነሳሽነት " ሸክዋ
አል አላህ !" "ጥያቄ በደል ብሶታችን ለፈጣሪ እናቅርብ!" በሚል ረመዳን ሊገባደድ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት
በሶሥት አውቶቡስ ከጣይፍ ወደ መካ በመጓዝ በህብረት ጸሎት ያደረጉት እንቅስቃሴ በረመዳኑ የተከሰተ የብዙዎቻችን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡
ኢድ ሙባረክ
ዛሬ ቅዳሜ የረመዳን ጾም የመጨረሻ ቀን ነው፡፡ ዛሬ ይሆናል ተብሎ ትናንት
በአብዛኛው የተገመተው የኢድ አልፈጥር ታላቅ በአል ለነገ ተላልፏል፡፡ ላለፉት አንድ ወራት የረመዳንን ውሎ ቅኝቴ ሙሉ ትኩረት ቀልብ
ወደሳበው የኢትዮጵያውያን ሙስሊማን እንቅስቃሴ ማድረጌ ያለ ነገር አይደለም፡፡ ያን አንስቸ ይህንን ጥየ ለማጋጋምም ሆነ ለማለሰለስ
አይደለም ! ሳውዲ ሆኖ ሃገር ቤት እየሆነ ባለው ሂደት ነፍሱ ስትሰቀዝ ያየሁትን ወገን ትክክለኛ ስሜት ለማስረዳት ያህል በማሰብ
ነው፡፡
ለኢድ ዝግጂት
እንደ ረመዳኑ ዋዜማ ሽር ጉዱ ብዙ ነው ፡፡ በኢድ ህጻናት አዲስ ልብስ ለብሰውና አዲስ ጫማ ተጫምተው ኢድን ርችት እየተኮሱ ይቀበሉታል፡፡
ዘመድ ጥየቃውና የሚሸጎጥላቸውን ገንዘብ ቆጣጥረው የሚዎዱትን መጫዎቻ የሚገዙበት በኢድ ነው ፡፡ ከወላጅ ዘመድ አዝማድ የተበረከተላቸውን
ገንዘብ ቋጠረው ወደ መዝናኛ ቦታና ሽርሽር የሚያዘወትሩበት የኢድ
በአል ትልቅ ትርጉም አለው ! ህጻናት በኢድ ከርሜላ ቸኮላት እየተለዋወጡና እየቃሙ ፤ ጭማቂያችውን እየመጠመጡ ከጓደኞቻቸው ጋር ተገናኝተው
አብረው ይቦርቃሉ ! በህጻናት ግርግር በታደመውን ቤት እየደመቀ በአሉን ለማክበር የታደለ የቡና ስርአቱም እንደ ሃገር
ቤት ነው ፡፡ የቤቷ እመቤት አለያም ባለተራዋ የቤተሰብ አባል ቄጠማ ነስንሳ፤ ፈንድሻውን ቆልታ ፤ቡና አፍልቶ በከርቤ እጣኑ ቤቱን እየታወደ በአሉ በመላ ቤተሰቡ በስላምና በጤና ይከበራል ! በዚህ መስሉ በአል ሙስሊም በአሉን ሲያከብር ክርስርያኑ ጎረቤትም አብሮ በአሉን እኩል ያከብራል፡፡ በሃገራችን በአንድ መኖር ያልቻልን ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን በጉርብትና ሲኖሩ በመከባበር የኢድ በዓል ሲያከብሩ ማየት ፍጹም የተለመደ ነው፡፡ የሃይማኖትና የዜግነት መለያየት ሳይታይ በአሉ በድምቀት ይከበራል፡፡ እዚህ ሳውዲ አረቢያ ስኖር ያየሁትና እያየሁት ያለሁት ይህንኑ እውነታ ብቻ ነው ! ይህ መሰሉ የአብሮነት ልምድና አኩሪ ባህል ምን ያህል እንደሚያስደስት ለማረዳት እንደኔ ጋዜጠኛ ቀላዋጭ ሆነው ከበአሉ ዋዜማ እስከ በአሉ መባቻ የበርካቶችን በር ማንኳኳትና መቅረጸ ድምጽን ይዘው መጠየቅ ግድ ይልዎታል ! የፈጣሪ ፈቃድ ከሆነ ዛሬም በዋዜማው አስተያየት ለመሰብሰብ ወደ ገበያው ወደ መዝናኛውና ወደ አባዎራዎች ቤት ጎራ እላለሁ ! ያየሁ የሰማሁት የደስታ መግለጫና የአበሉን አንድምታ በተለመደው የጀርመን ራዲዮ ዘገባየ አቀርበዋለሁ ! ለሁሉም ከረመዳን እስከ ኢድ ዋዜማ
ያነሳሁ የጣልኩትን ቅኝቴን የምቋጨው በአሉ የሰለም የጤናና የብልጽግና ይሆንላችሁ ዘንድ መልካም ምኞቴ በመግለጽ ነው !
መልካም በአል
! ኢድ ሙባረክ !
ነቢዩ ሲራክ
No comments:
Post a Comment