በእኒህ ወጣት ሙስሊም ወንድሞቻችን ላይ እየሆነ ያለው እጅግ በጣም ያሳዝናል
! የሙስሊም ወንድሞቻችን ላይ በግፍ መታሰርና አስከፊ አያያዛቸው
ያበሳጫቸው በአረብ ሃገር የሚኖሩ ክርስትያንና ሙስሊም ወንድሞች ስልክ በመደወል የተሰማቸውን ሃዘን በተደጋጋሚ ገልጸውልኛል፡፡ ብዙዎች ጉልቻ ቢቀያየርም ወጡ አልጣፍጥ ብሏል
እያሉ ይመስላል . . . . ጃንሆይ አውግዘን ደርግን ባመጣን ማግስት በርቀት የሰማነው ሁሉ የአፈና ፤ የግድያና የሰቆቃ ዘመንን በራሳችን ላይ ተጫነብን ! ከ17 አመት መሪር ትግል በኋላ
ደርግን አሽቀንጥረን ጣልን . . . ይህው ላለፉት ሃያ አንድ አመት ሀገሪቱ በአንድ አውራ ፓርቲና በአንድ መሪ ስትመራ ፓርቲው
ታገልኩለት ያለ ዲሞክራሲና ነጻነት ማግኘት አልቻልንም ! ሌላው ቀርቶ የፕሬስ ነጻነት አንድ አፍታ ታይቶ ጠፋ እንጅ አልቀጠለም
! ያለመታደል ሆኖ ነው መሰል ደርግ በተቃዋሚው ላይ አደረገ ስንል ስናዎግዘው የነበረው እስራት ፤ የአፈና ፤ አሰቃቂ ድብደባ ፤
የግድያና የሰቆቃ ጊዜ አላከተመም !
ይህን
ሁሉ ያስታወሰኝ በኮሚቴዎ ደረሰ የተባለው ድብደባ እስራትና የምሽቱ የኢቲቪን ዜና ነበር ፡፡ ዜናውን እንደለመድኩት እያመመኝ ሰማሁት፡፡ ብቻ ፈጣሪ ይህችን ሐገር ጥሎ አይጥላትም እንጅ በመንግስት
መገናኛ ብዙሃን በሚቀርቡ ውልን ያሳቱ መረጃዎች ምን ያህል አብዛኛውን ንጹህ ህዝብ በጥፋት ማዕበል ሊያሰልፍ እንደሚችል ሳስበው
አዘንኩ ! በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊም ምዕመናን መረጥናቸው ያሏቸው
ኮሚቴወች እየታደኑ ሲያዙ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በተለይም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚያቀርባቸው ኮሚቴውን "ጽንፈኛና አክራሪ"
እያሉ የሚያወግዙ ሰላማዊ ሰልፎች በያዝነው ሳምንት ለእርምጃ እንዲመቹ ተደርገው እየተበራከቱ ሄደዋል፡፡ ማለዳ ላይ በስልክ ወደ
ሃገር ቤት ስደውል ያገኘሁት ወዳጀ የጎንደርና የጎጃም ሙስሊማንም ሰላማዊ ሰልፍ ውጡ ተብለው በየቀበሌው በግዴታ መቀቀሳቸውን ሲያጫውተኝ
ስላማዊ ሰልፉን ለማይሳተፉ ከስኳር እደላው እንደሚገለሉ እንደተነገራቸው አጫውቶኛል፡፡ ሃይል እስካለ ድረስ ተፈላጊዎችን ማሰርና
እየሆነ ያለውን ማድረግ እየተቻለ ሰላማዊውን ነዋሪ ቂም ሊያቃባ የሚችል ፕሮፓጋንዳ ለምን እንዳስፈለገ አልገባኝም፡፡
በሰለጠነው በዚህ በኛ ዘመን ከሃያ አንድ አመት በፊት የደርግን ዘመን መልሸ መላልሸ ለማስታዎስ ተገደድኩ . . .ደርግ ጭንቅ
ሲለው ህዝብን ማስተባበርና ማዝመት ሲያሻው ብቻ ሳይሆን ጥላቻን ሲዘራብን የዛሬውን መንግስት ባለስልጣናት የአጥፍቶ ጠፊ ደቀ መዛሙርት
ያደርጋቸው ነበር፡፡ በደርግ "የሻቢያና ወያኔን ሀገር ገንጣዮች እናዎግዛለን " በሚል
በመጨረሻዋ ሰአት ሳይቀር ይተወን የነበረውን ያላታደለውን የኢቲቪ የያኔ ዘገባ ከፊት ከፊቴ ድቅን አለ . . .ዛሬም አብዛኛው ድጋፍ
እያገኑ የመጡትን "ጽንፈኛና አክራሪ" ኮሚቴዎች እያስባለ
የሚኬደውን መንገድ ሳስበው ከቀናት በፊት በአንዋር መስጊድ ተሰባስበው በሰላማዊ መንገድ "መሪዎቻችን ይፍቱ !"
የሚል ድምጽን የሚያሰሙ ወንድሞቻችንን ውሎ ከሚያሳዩት ተንቀሳቃሽ ፊልሞች መካከል 12 ደቂቃ በሚሆነው በአንዱ ፊልም ያየሁት የወገን
ድምጽና የምሬት እንባ መንፈሴን አሰቃየው ! እውንም ይህ ሰላማዊ
የመብት ጥያቄ "ጽንፈኛና አክራሪ"ነት ነው ተብሎ ፕሮፓጋንዳ ሊሰራበት ይገባ ነበርን ? ስል ራሴን ብጠይቅም መልስ
አላገኘሁም ! ለነገሩ በአንባገነኖች መንደር ይህ መሰል ፕሮፓጋንዳ የተለመደ መሆኑን ላፍታ አዘከርኩት ! አዎ በአረብ ሀገሩ አብዮትም
ይሰራ የነበረው ፕሮፓጋንዳ ይህን መሰል የማይጨበጥ ነበር ፡፡ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ፕሮፓጋንዳ ሌላ ፤ እውነቱና እየሆነ ያለው ሌላ ለመሆኑ በጋዳፊዋ ትሪፖሊ ፤ በሙባረክ ካይሮ ፤ በአሊ አብደላ ሳላህ ሰንአና በበሻር ደማስቆ ያየነውና እያየነው ያለው በተመሳሳይ
ሁኔታ የተቀነባበረው ትዕይንት ተመልክተናል ! ትናንት በጃንሆይ የጃንሆይን ካባ ፤ በድርግ የደርግን ካባ ደርቦ እንዲያ ሲያቦኩ
የነበሩት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘርፎች ዛሬ የኢሃዴግን ካባ ደርቦ ተመሳሳይ ስራቸውን ሲገፉት ያለንበትን የሰለጠነ አለም ከግምት
ያስገቡት ቢሆን ምንኛ ደግ ነበር ! የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ያሻቸውን ሲደሰኩሩ እድሜ ለሰላጠነው ቴክኖሎጅ በቅርቡ የአንዋርንና የአዎልያን ግጭት ተከትሎ ዩትዩብን በመሳሰሉ በተለያዩ
ድህረ ገጾች የተለቀቁ ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ፊልሞች እያወጡት ያለው መረጃ
የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ራቁት ያስቀረ ሃቅ ለመሆኑ ፊስ ቡክን ከፈት አድርጎ አንዳፍታ መመልከት ብቻ ይበቃል ! ይህን
ሁሉ አዙሮ ላየው በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሃገሩ በነጻነት እየኖረ ነው ለማለት የሚያስደፍር ነገር ይኖር ይሆን ! ?
No comments:
Post a Comment