ፕሬዚደንት
መሐመድ ሁስኒ ሰይድ ሙባረክ ማን ናቸው ?
ሾተል - ከባህረ ሰላጤ
በፈርኦን ምድር
የማይቀረው የፍርድ ቀን እውን ሲሆን !
 |
ሁስኒ ትናንትና ዛሬ
|
ሁስኒ
ሙባረክ ግብጽ ካፈራቻቸው ሃገር ወዳድ ቀዳሚ የክፉ ቀን ልጆች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ሁስኒ የሀገራቸውን ድንበር ላለማስደፈር
በከፈሉት የጀግንነት ውሎ ክብር ከኒሻንና ሜዳሊያ አልፎ የመራሄ መንግትስነትን ስልጣን የተቀዳጁ መሪም ለመሆን የበቁት በአጭር
የግልጋሎት ዘመን ነበር፡፡ ይህ ክብር ዝናቸው በአጭር ጊዜ በግብጽ ህዝብ ዘንድ ያስከበረ ያስወደዳቸው የግብጽ ጀግና አርበኛ
ነበሩ፡፡ ይህ ሁሉ ግን ትናንት ነበር ! ዛሬ ሁስኒ ሙባረክ ስም ክብር ዝናቸው ደስ አይልም፡፡ ዝና ክብራቸው አሽቆልቁሏል፡፡ ዛሬ
እንደ ፈርኦኗ ሀገር የቁርጥ ቀን ጀግና በኩራት አንገታችውን ቀና አድርገው ለመታየት አልተቻላቸውም፡፡ በተለይም ከስልጣን
ከተዎገዱባቸው ካለፉት በርካታ ወራት ወዲህ ሁስኒ በመጨረሻው ሰአት የሰሩት ግፍና በደል አንገታቸውን አስደፍቷቸዋል፡፡ ሁስኒ
ሙባረክ በአንባገነንነት የህዝቡን ነጻነት ረግጠውና አፍነው እየገዙ ስለግብጽ ማደግ መመንደግ ከሃገር አልፎ በአለም አቀፍ
መድረኮች ይደሰኩሩ ያስደሰኩሩና እንቢልታ ያስጎሰሙ ነበር፡፡ ሁስኒ በረጅሙ የአገዛዝ ዘመናቸው ግብጻውያንን የነጻነትን ልቻሉ፤ ከችጋርና ከድህነት ያልታደጉ መሪ በመሆናቸው ግፍን አልቀበልም
ባሉ በዘመናችን ቆራጥ ግብጻውያን ወጣቶች ተጋድሎና በህዝብ ርብርብ ከስልጣን ተወግደዋል፡፡ ከዚያም ወዲህ ወህኒ ወርደው በውስጠ
ደዌ በሽታ ተቀስፈው እንኳ ፋታ የሰጣቸው የለም፡፡ ነጋ ጠባ በቃሬዛ ተጋድመው እየተጎተቱ እንደወንጀለኛ በብረት አጥር ተከልለው
የሰሩትን ግፍ ሳይወዱ በግድ እየመረራቸው አድምጠዋል፡፡ የቀድሞ ጓዶቻቸው እነ ፊልድ ማርሻል ጀኔራል ሁሴን ታንታዊ ፍርዱን
ምክንያት እየሰጡ ቢያዘገዩትም ሊሸፍኑ ሊደብቋቸው አይቻላቸውም፡፡ ሁስኒ
ስልጣንን ሙጥኝ
ብለው በምርጫ ስም እያታለሉ በወታደርና በደህንነት ሃይል እያንቀጠቀጡ ገዝተዋልና ዛሬ እንደ ቁርጥ ቀን አርበኛ መሪ ሳይሆን እንደ ቀማኛ ነብሰ ገዳይ ይፈረድባቸው ዘንድ
ግብጻውያን ከዳር እስከዳር ያሰሙት ድምጽ ሰሚ አግኝቷል፡፡ ሁስኒ በቅቤ ምላሳቸው ደልለው በአምባገነን በትራቸው የቀጠቀጡ መሪ ናቸውና ለአመታት ከተንፈላሱበት የአምባገነን ስልጣን ወርደው በተራቸው
በሰሩት ወንጀል የእድሜ ልክ እስራትን ሰኔ ሳይጠባ ተከናንበዋል፡፡
እናም የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ
እንደ ኢራቁ ፕሬዚደንት ሳዳም ሁሴን ፍርድ ፊት ቀርበው ብይን የተሰጣቸው መሪ በመሆን በሰፈሩት ቁና ተሰፍረዋል ! ሁስኒ ፍርድ
ከተሰጣችው ወዲህ ጤና አጥተው የከረሙት ፕሬዚደንት ሁስኒ የጤና ሁኔታ አደጋ ላይ እንዳለ ይህን ጽሁፍ ሳዘገጃጅ የመገናኛ
ብዙሃን ዘገባዎች ወሬውን እየተቀባበሉ በመናኘት ላይ መሆናቸን ታዝቤያለሁ፡፡ ለመሆኑ የግብጽ የቁርጥ ቀን ልጅ ከሆኑት ታላላቅ
የግብጽ መራሄ መንግስታት የሚመደቡት የቀድሞው ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ ከቶ ማን ናቸው ? ከአረቡ አለም የጸደይ አብዮት ወዲህ
ስለ ግብጽ የቁርጥ ቀን ልጆች ማስዳሰስ የጀመርኩትን የታሪክ ቅኝት አጠቃልላለሁ ፡፡ በዚህ የመጨረሻ ቅኝቴ በረጅም የአረቡ
አለም ቆይታየ ስለ ቀድሞው ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ ከአረብ አባቶች ፤ ከታሪክ ተመራማሪዎች ፤ ከማህበረሰቡና ከታሪክ መዛግብት
ያገኘሁትን መረጃ እንጂ የታሪክ ተማሪ አለያም ተመራማሪ ሆኘ ግን አለመሆኑን አንድ ትሉ ዘንድ ግንዛቤ ከሰጠሁ የዛሬ ቅኝቴን
ልጀምር ! የፈቀዳችሁ ተከተሉኝ . . .
ሁስኒ ሙባረክ ማን ናቸው ?
 |
| የቁርጡ ቀን ሰው |
 |
| ወጣቱ መኮንን ሁስኒ |
እ.ጎ.አ ሜይ 4 ,1928 በሙኑፊያ ግዛት በሚያዋስነው በአባይ
ወንዝ ዳርቻ ሽቢል አልኩም በምትባል መንደር የተወለዱት ሙሃመድ ሁስኒ ሰይድ ሙባረክ እንደ ቀደምቱ ፕሬዚደንት ጀማል
አብድልናስርና ፕሬዚደንት አንዋር ሳዳት መካከለኛ ገቢ ካላቸው ግብጻውያን ቤተሰቦች እንደመጡ ዝክረ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ ሁስኒ ሙባረክ በአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተገቢ ሁኔታ አጠናቀው ወደ ግብጽ አየር ሃይል አካዳሚ በመግባት
የመጀመሪያ ባችለር ዲግሪያቸውን በ1949 ገና በወጣትነት እድሜያቸው ያገኙ ትጉህ ተማሪም ነበሩ፡፡ ሁስኒ በአየር ሃይል ንቁ ተሳትፏቸውን
አንድ ብለው የጀምሩት በአብራሪነት ተመድበው መስራት ከጀመሩ ወዲህ ሲሆን ከዚህ ጊዜ አንስቶ በተለያዩ የአየር ሃይሉ ሃላፊነት ክፍሎች
አገልግለዋል፡፡ የአየር በረራ ሙያቸውን ለማጠናከር ወደ ሶቭየት ህብረት በማምራት ከፍተኛ የሆነ ስልጠናን ያገኙ ሲሆን ከ1966
እስከ 1967 በካይሮ ምዕራብ አየር ሃይልንና የቢኒ ሱዊፍ አየር ሃይልን በዋና ሃላፊነት ከዚያም በኋላ በአየር ሃይሉ ባሳዩት የሙያ ብቃት በወጣትነት እድሜያቸው እ.ጎ.አ
በ1972 የግብጽ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሆነው በፕሬዚደንት አንዋር ሳዳት ተሹመዋል፡፡ ሁስኒ ብዙም ሳይቆዩ በ1973 የጥቅምቱ አብዮት ባሳዩት የአመራር ብቃት በአጭር ጊዜ የአየር
ሃይል ጠቅላይ አዛዥና ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ስልጣን በተሰጣቸው በአጭር የጊዜ ልዩነት እ.ጎ.አ አፕሪል 1975
በወዳጃቸው የፕሬዚደንት አንዋር ሳዳት ምክትል በመሆን በመሾም የአንዋር የቀኝ እጅ ሆነው ዘለቀውም ነበር፡፡
የፕሬዚደንት አንዋርን ሳዳትን
የውጭ ግንኙነት ክፍተት የጠገኑት ሁስኒ. . .
ምክትል ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባርክ
ፕሬዚደንት አንዋር ሳዳት ከእስራኤል ጋር የተስማሟቸውን ስምምነቶች ተከትሎ ከአረብ ሃገራት ጋር ያላችው ግንኙነት አደጋ ላይ
ሲዎድቅ አፈፍ አድርገው በማንሳት ትልቅ ሚና መጫወታቸው ይወሳል፡፡ ፕሬዚደንት አንዋር ከእስራኤል ጋር ያደረጉት ስምምነት በሃገር
ውስጥ ጽንፈኞች ዘንድ ከፍ ያለ እክል ሲገጥማቸው ጽንፈኞችን በመደገፍ የሚጠረጠሩትን አጋር አረብ ሃገራት በማግባባቱ ረገድ
ሁስኒ ሙባረክ ላቅ ያለ ስራ ሰርተዋል፡፡ ከአረቦች ጋር ሆድና ጀርባ ያደረጋቸው የፖለቲካ ትኩሳት ሙቀቱን ለማብረድና ያኮረፉት
የአረብ መንግስታት ለማግባባት መድሃኒት ማርከሻው ምክትል ፕሬዚደንቱ ሁስኒ ሙባረክ ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ ወደ ሶርያ ደማስቆ ዘልቀውም
ከሶሻሊስቱ የሶርያ ፕሬዚደነት ሃፊዝ አል አሳድ ጋር ያደረጉት ማግባባት ተቀባይነትን ባያስገኝላቸውም ሪያድ ሳውዲ አረቢያ
መጥተው ከሳውዲ አረቢያን ልኡላን ጋር ያደረጉት ምክክር እንደሰመረላቸው የታሪክ መዛግብትና የወቅቱን መሮጥ በአግራሞት
የሚያዘክሩት አረባውያን አባቶች አጫውተውኛል፡፡ ሁስኒ ሙባረክ በምክትል ፕሬዚደንትነት ዘመናቸው በግብጽ እስራኤል ጦርነት ወቅት
አየር ሃይሉን በመምራት የከፈሉት መስዋዕትነት ስኬት ከሃገረ
ግብጽ አልፎ አረቦችን ሳይቀር ያኮራ ነበር፡፡ ይህም ከአረቦች ጋር ለሚደረገው ዲፕሎማሲው ረገድ ያደረጉት ሁሉ እንቅስቃሴ እንዲረዳቸውና
ውጥናቸውን እንዳሰመረው ብዙ መረጃዎችን እያጣቀሱ መናገር ይቻላል፡፡ በፕሬዚደንት አንዋር ሳዳት ከእስራኤል ጋር ያደረጉትን ስምምነት ተከትሎ
አረቦች ያነሱትን ተቃውሞ ለማረቅ የሙባረክ ክብርና ዝና ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው በሁስኒና በግብጽ ዙሪያ መረጃ ሳሰባስብ
ያነጋገርኳቸው አረባውያን የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ከረጅም ግልጋሎት በኋላ አሁን በጥሮታ ላይ የሚገኙት የቀድሞው የሳውዲ
ንጉስ ፋድ ቢን አብድላዚዝ አማካሪና በንጉስ አብድልአዚዝ ዩንቨርሲቲ የፓለቲካ ሳይንስ ዲን የነበሩት ፕሮፌሰር መሃመድ ዘይኑ ከክብ
ፊታቸው ላይ የተነሰነሰውን ነጭ ጺማቸውን እያሻሹ ስለግብጽንና በመንበረ ስልጣኑ ስላለፉት መሪዎች የሚያወሱት በልዩ ስሜት ነው፡፡
ፕሮፌሰር መሃመድ ዘይኑ ከንጉስ ፋሩቅ ንጉሳዊ አገዛዝ በኋላ ነጻ የወጣችውን ግብጽ የመሩ መሪዎች አምባገነንነት ቢሆኑም እንኳ ግብጾች ረግጠዋቸውም ቢሆን ብሄራዊ
ማንነታቸውን ለሚያጎሉ መሪዎቻቸው ያላቸው ክብር ከፍ ያለ እንደሆነ እንዲህ ይገልጹታል ". . . ግብጾች ለጀግኖቻቸው
ክብር አላቸው ! መሪዎችም ምንም ያህል አምባገነን ቢሆኑ የዜጎቻቸውን ብሄራዊ ጥቅም በማስከበሩ ረገድ የሚስተካከላቸው የለም፡፡
ግብጽ መሪዎች አጥታ አታውቅም ! መሪዎቿ ከሚሰሩት ትልቅ ነገር ዜጎችን የቱንም ያህል ቢጨቁኗቸውም ብሄራዊ ማንነታቸውና
ኩራታቸው እንዲነካ ግን አይፈልጉም ፡፡ በየትም ሃገር የሚኖር ግብጻዊ ለሃገሩ ያለው ፍቅርና ክብር የሚመነጨው ከዚህ
ይመስለኛል፡፡ " ሲሉ በግብጽ ጨቋኝ ወታደራዊ መሪዎችና
በሃገሬውን መካከል በባንዴራቸው ስር ያላቸው መልካም ግንኙነት እንደሚያስደምማቸው ዘርዘር አድርገው ሲያወጉት ያስደስታል፡፡
በሳውዲ አረቢያ ጅዳ ነዋሪ የሆኑትና ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ስዘዋዎር ከማገኛቸውን በርካታ ግብጻውያንም የተረዳሁትም
ይህንን ሃቅ ነው፡፡
የሁስኒ በትረ ስሎሞን መጨበጥና ሁስኒን እዚህ ያደረሳቸው መንገድ . . .
 |
| የያኔው ትንታግ መሪ |
ምክትል ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ እ.ጎ.አ ኦክቶበር 6.1981 ፕሬዚደንት አንዋር
በወንድማማች እስላሞች ቡድን ተጠርጣሪ ጽንፈኞች ጥይት ሲገደሉ ከአጠገባቸው ነበሩ፡፡ ሁስኒ የወዳጃቸው የፕሬዚደንት ሳዳትን
አስከሬን አፈር አልብሰው በተመለሱ በጥቂት ቀናት ልዩነት በጊዜያዊነት የተቆናጠጡትን በትረ ሰለሞን እ.ጎ.አ ኦክቶበር
13.1981 የግብጽ ፓርላማ ከፍተኛ ድምጽ አልተለያቸውም ነበር፡፡ ድምጹን ተከትሎም ፓርላማው ግብጽን ይመሩ ዘንድ ምክትል
ፕሬዚደንት ሁስኒን በማያሻማ ሁኔታ 98.5 በሆነ ድምጽ አጸደቀላቸው! ከጥቂት የሳዳትን ገዳይ ከሚባሉት ጽንፈኞች ውጭ
ከፓርላማውና አልፎ ተራው ግብጻዊ ይሁንታን አግኝተው ስልጣናቸውን ተረከቡት ፡፡ በትረ ሰለሞናቸውን በኩራት ሁስኒ ሙባረክ
ስልጣን ከተረከቡ ጀምሮ በቀጣይ አስርት አመታት በኢኮኖሚው ዘርፍ ግብጽ እምርታ እንድታሳይ እገዛ ያደረጉ በርካታ መሰረታዊ
ልማቶችን ማካሄዳቸው የሚካድ አይደለም፡፡ ለኢኮኖሚው ማደግ ዋንኛ ቁልፍ ነው የተባለውን የግል ባለሃብቶ ለሚያደርጉት ማናቸውም
እንቅስቃሴ በሙባረክ አስተዳደር ከፍተኛ ድጋፍ ሲደረግላቸው የተራው ሰራተኛ መብት ሲረገጥ ሰሚ የመጥፋቱ አንድምታ የመንግስት
ካቢኔውና ማዕከላዊው መንግስት ከማይወጡበት ዳጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡
ይሁን እንጅ ከጥቂት አመታት በኋላ ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ ከተወዳጅ መሪነት ወደ አንባገነን መሪነት እንደተቀየሩ
በተከታታይ አመታት በታዩት ምርጫዎች አሳዩ፡፡ በተለይም ነጭ ለባሽ የደህንነት ሳራዊታቸውን መከታ በማድረግ ፕሬዚደንት አንዋር
ሳዳት ሲገደሉ የወጣውን አስቸኳይ አዋጅ መከታ አድርገው ተቃዋሚዎቻቸውን ፤ የተቀናቃኝ ፓሪቲዎችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ
በማፈን፤ በማሰርና፤ በማንገላታት እየወሰዱት መጡ፡፡ ይህም ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተጣምሮ ሁስኒ በግብጽ ህዝብ የነበራቸውን ዝና
ያኮሰው ገባ፡፡ ፕሬዚደንት ሁስኒ በጦር በጠመንጃ አፈሙዝ በመመካት እያደሩ አምባገነን እየሆኑ ሲመጡ ነገር እየተበላሸ መጣ፡፡ አምባገነን እየሆኑ ከመጡናቸው ከ1990ዎቹና በተከታታይ አመታት የሃገሪቱ
ኢኮኖሚ ማደግና መመንደግ በነዋሪው ኑሮ መሻሻል ዙሪያ የታየ ነገር አለማሳየቱ ነዋሪውን ሰላም አሳጣው፡፡ የስራ ፈት ግብጻውያን
ቁጥር እያደገ መምጣትና የኑሮ ውድነት አብዛኛው ኑሮ ከእጅ ወዳፍ የሆነው ነዋሪ ኑሮ እየከፋ ሲመጣ የአብዛኛውን ነዋሪ ጥያቄ
በሙባረክ አስተዳደር ትኩረት አልተሰጠውምና የሁስኒ ሙባረክ መንግስት ወደ ማይወጣበት የፖለቲካ ዳጥ ተዘፈቀ ! በ1995 የጆሃራአላል ነይሩ አለም አቀፍ ሽልማት ያገኙ መሪ የመሆናቸውን
ያህል Parade Magazine ፓራድ የተባለው አለም አቀፍ መጽሄት በ2009 ባወጣው እትሙ ደግሞ በአመታት ልዩነት
ወደ አንባገነን ተቀይረው በአለማችን ካሉት ቀንደኛ አንባገነኖች መካከል የ20ኛውን ቦታ መያዛቸውን የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡
ግብጽ አሜሪካና የባህረ ሰላጤው የኢራቅ ጦርነት. . .
 |
| ሁስኒና ቡሽ |
የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ነዳጅ አምራች ሀገራትን
ለመቀራመት አሜሪካና ምዕራባውያን ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ጀምሮ በአደባባይም ሆነ በስውር አቅማቸውን በማሰባሰብና በረጅሙ
የስለላ መረጃ አፍንጫቸውን በማሾል ሲያነፈንፉ የተነሱበት ወቅት እንደነበር አረብ ጸሃፍት ይናገራሉ፡፡ ቀልባቸው ከነሆለለው
መካከል እንደ አሜሪካ የባተለ ስለመኖሩ ግን በእርግጠኝነት የሚናገር የለም ማለት ይቻላል፡፡ እናም አሜሪካኖች በግብጽ ከአንዋር
ሳዳትን ከእስራኤል ጋር በማስታረቅ የጀምሩትን የቀለጠ ጉድኝት በፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ ሰላሳ ሁለት አመታት ጊዜም አሳክተው
እንደቀጠሉበት የታሪክ መዛግብት ያወሳሉ፡፡ ከመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ጀመሮ እንደኔው እድሜ አራት አስርት አመታትን ሊደፍኑ
ሶስት አስርት አመታትን በተሸጋገሩባቸው ጥቂት አመታት የመጨረሻዋ ሰአት ድረስ አሜሪካና ሙባረክ የአንድ ሳምንቲም ሁለት ገጽታ
ነበሩ፡፡ ከመልካም ጉድኝነት አልፎ ግብጽ ደጎስ ያለ በቢሊዮን የሚቆጠር የማይነጥብ ጉርሻ ማግኘት የጀመሩትም በሙባረክ ዘመን
ነገር፡፡ የአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ መንሰራፋት ሲወሳ ግብጽ በዋናነት ሳውዲና ዮርድያኖን በቅደም ተከተል ይወሳሉ፡፡
ለዚህ ሁሉ የአሜሪካ የረቀቀ የመስፋፋት ሴራ በመካከለኛ ምስራቅ ሃገራትን በማባበሉ፤ በማስፈጸምና በማስደቆሱ ረገድ የሹፌሩን
ቦታ እንደ ያኔው ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ የተቆጣጠረው እንዳልነበር የቅርብ ጊዜ ታሪክ እያጣቀሱ መናገር ይቻላል፡፡ የዚያን
ዘመን የመካከለኛው ምስራት ሃያል ፤ የአንበሳ ግርማ የነበራቸው አስፈሪው መሪ የቀድሞው የኢራቅ ፕሬዚደንት ሳዳም ሁሴንን
ከስልጣን ለማውረድ ታቅዶ የኒኩልየር ጦር መሳሪያ ክምችት ስም ሲለጠፍበት አረብ ወንድማቸውን ለማንበርከክ ከአሜሪካ ጎን
በመሰለፍ በፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ የምትመራውን የፈርኦን ምድር ግብጽን የቀደመ አልነበረም፡፡ የአረቡ ግርማ ሞገስ የባግዳዱን
ባለግርማ አምበሳ የፕሬዘደንት ሳዳምን ከስልጣን መወገድ የአሜሪካ እጅ አለበት በሚለው ለሚስማማ ሁሉ የግብጽ እጅ ከፍ ያለ
እንደነበር ሃቁን ይስተዋል አልልም፡፡ በባህረ ሰላጤው ጦርነት ለሃገራቸው ለግብጽ ደጎስ ያለ ጥቅም ያስገኙት ፕሬዚደንት ሁስኒ
ሙባረክ ነበሩ በሚለው ማስረገጫ ሃሳብ የምንለያይም አይመስለኝም ! ከሁሉም የሚገርመው የሁስኒ ሙባረክ የዲፕሎማሲ አካሄዳቸው ሲሆን በባህረ
ሰላጤው ጦርነት ቀዳሚ የአሜሪካ አጋር የነበሩት ፕሬዚደንት ሙባረክ በ2003 በኢራቅ ላይ ዳግም የጦርነት ከቀድሞው አቋማቸው
ተንሸራተዋል፡፡ በኢራቅ የክተት አዋጅ እንቢልታ ሲመታ ሙባርክ ስምጻቸውን በተቃውሞ አሰሙ፡፡ " . . .እየከረረ
የመጣው የእስራኤልና የፍልስጣኤም ጦርነ ከፈመታቱ አስቀድሞ ጦርነቱን መደረጉ አግባብ አይደለም፡፡ " በማለት ጦርነት
ወረራውን እንደማይደግፉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል፡፡ "ጦርነቱ ቢከፈት ውጤቱ ኦሳማ ቢላዲንን መሰል በመቶዎች
የሚቆጠሩ ጽንፈኞችን ከመፍጠር ባለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው !" ሲሉ ለወዳጆቻቸው ለአሜሪካና ምዕራባውያን ግልጽ
አቋማቸውን በማሳየት ተቀባይነት የሌለው ምክር ለግሰዋል፡፡
በሙባረክ ላይ የተቃጡት የግድያ ሙከራዎች . . .
 |
| የግድያው ሙከራ ዜና ከኛው ቤት |
በፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ እ.ጎ.አ በ1995 በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ በተገኙበት
አጋጣሚ የተደረገባቸውን አደገኛ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው ሲሆን ከዚያም በኋላ እ.ጎ.አ በ1999 በሃገር ውስጥ ሰይዲ ተብሎ
በሚታወቅ አንድ የወደብ ከተማ በሰላ ጩቤ የግድያ ሙከራ ተቃጥቶባቸዋል፡፡ ሙባረክ እኒህን የግድያ ሙከራዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ
ስድስት ያህል የግድያ ሙከራዎች ተቃጥቶባቸው ከሁሉም ቅስፈቶች አምልጠዋል፡፡ ታዲያ ሁሉንም የግደያ ሙከራውን እንዳቀነባበሩ
በከፍተኛ ደረጃ የሚታመኑት በፕሬዚደንት አንዋር ሳዳት የገደሉትና ሁስኒ ወደ ፍርድ ለማቅረብ አነጣጥረው ያሳድዷቸው
የነበሩ በስውር ይንቀሳቀሱ የነበሩት የሙስሊም ወንድማማቾችና
የጀሃድ ጽንፈኛ አባላት እንደሆኑም ይታመናል፡፡
የ2005 ምርጫ ፤ ተሃድሶ ፤ የፕሬዚደንት ሁስኒ ያፈጠጠ አምባገነንነት . . .
 |
ዶር አይመን ኑር
|
ፕሬዚደንት ሙባረክ በትረ ሰሎሞናቸውን ከተረከቡ ወዲህ እ.ጎ.አ በ1987. በ1993 በ1999 እና በ2005 ለአራት
ተከታታይ አመታት ምርጫ አካሂደዋል፡፡ ያም ሆኖ ምርጫው ማደናገሪያ እየሆነ አብዛኛውን ድምጽ አገኝተው አሸነፉ እየተባለ
በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስም ህዝብ አዳምን ያታለሉ የግብጽ ብቸኛ መሪ ነበሩ፡፡ ሙባረክ በተደጋጋሚ ምርጫዎች ይህን መሰል
ማጭበርበር ማድረጋቸው በተቃዋሚዎቻቸው በማስረጃ በመጋለጡ የምርጫ ሂደት ተሃድሶ ይደረግበት ዘንድ በሃገር ውስጥና በአለም አቀፍ
ደረጃ ጉትጎታ በኋላ ሙባረክ የሚያሽከረክሩት ፓርላማ ጫና አረፈበት፡፡ በቀጣይ ጊዜያትም የግብጽ የፖለቲካ ምህዳር ብዙሃን
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉበትና የፕሬዚደንት ተመራጮችም በብዙሃን ፓርቲዎች የተወከሉ ይሆኑ ዘንድ እ.ጎ.አ ፊብሩዋሪ
26.2005 ህገ መንግስቱ በፓርላማው ተሻሽሎ ጸደቀ፡፡ ይህ በጸደቀ መባቻ ሴፕቴምበር 2005 ብልጡ ፕሬዚደንት ሙባረክ
ራሳቸውን የፓርላማው ተመራጭ በማድርግ በአብላጫ ድምጽ ዋና ተመራጭነታቸውን አጸኑ ፡፡ ጁላይ 20. 2005 ለፕሬዘደንት ምርጫ
እንደሚቀርቡ ለህዝብ ይፋ አደረጉ፡፡ ሴፕቴምበር 2005 በተደረው ምርጫ የተሻሻልውን ህገ መንግስት በሚያዘው መሰረት ብዙሃን
የፕሬዚደንትነት መራጮች ያሳተፈ እንዲሆን ቢደረግም ስልጣን ጥመኛው ሙባረክ ግን ምርጫውን በእጃቸው ለማስገባት ወታደራዊ
የማይገሰስ ስልጣናችውን መከታ እያደረጉ ስራዎችን በስውር መከወንን ያዙ፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑን፤ በጸጥታ አስከባሪዎች፤ ዋና ዋና
የመንግስት መገናኛ ዘዴዎች (ቴሌቪዥን፤ ራዲዮና ጋዜጣ) ፤ የመንግስት ተሽከርካሪዎችንና የተለያዩ ተቋማንትን ለምርጫቸው መሳካት
አዘጋጇቸው ፡፡ ለስውር ጉዟቸው ስኬት ተቃዋሚዎቻቸውን በማግለል የህዝብ ሃብቶችን ለግል ስልጣናቸው ማስጠበቂያ ተገለገሉባቸው፡፡
ብዙም ሳይቆይ እ.ጎ.አ ሴፕቴምበር 7.2005 በሃገረ ግብጽ በልዩ ሁኔታ ይደረጋል ተብሎ የተጠበቀው ምርጫ ፕሬዚደንት ሙባረክ
ባደራጇቸው አጭበርባሪዎች የመራጭ .ድምጽ እየተሰረቀ ፤መራጭ በገንዘብ እየተገዛ፤ በሌሎች ተመራጮችንና መራጮችን በማስፈራራት
በተከወነው ሴራ ፕሬዚደንት ሙባረ አሸናፊ ሆኑ ! በዚሁ ምርጫ ሙባረክ 10 ያህል ተፎካካሪዎቻቸውን ማሸነፋቸውን ይፋ አደረጉ፡፡
በዚሁ ምርጫ ከፕሬዚደንት ሙባረክ ጋር በተወዳዳሪነት የቀረቡት ዶር አይመን ኑር ተብለው የሚጠሩት የነገው ፓርቲ ፕሬዚደንት "ኢል ጋህድ " El-Ghad Party ዋና ሃላፊ ምርጫው የተጭበረበረ እንደሆነ በማስታወቅ ይደገም ዘንድ ቢጠይቁም ሰሚ
አላገኙም፡፡ ሰሚ ማግኘት ቀርቶ አጭበርባረው ስልጣን ያዙ የሚሏቸው የሙባረክ ምስለኔወች በቀጣይ ወራት ዲሴምበር 2005 ዶር
አይመን ኑርን በማጭበርበር ወንጀል ሸፍጥ ቀባብተውና በስራቸው በሚቆጣጠሩት ፍርድ ቤቶች አስመስክረው ለአምስት አመታት ያህል
ዘብጥያ ወረወሯቸው ፡፡ ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ እድሜያቸው እየገፋ እሳቸውን ተክቶ ግብጽን ያስተዳድር ዘንድ ልጃቸው ጀማል
ሙባረክን አዘጋጅተውም ነበር፡፡ እ.ጎ.አ በ2009 የበኸር ልጅ ጀማል ሙባረክ በግብጽ የፖለቲካ ህይወት ተሳታፊነቱ በግልጽ
እየጎላ እንዲመጣና በረቀቀ ስልት ቢያዘጋጁም አልተሳካላቸውም፡፡ ይህ መሰሉ በአምባገነንነት እየተወሰደ የመጣው የሙባረክ
መንግስት እርምጃ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም በአሜሪካ ውግዘት ቢያስከትልም ያመጣው ለውጥ ግን አልነበረም፡፡
አስቸኳይ አዋጅ ፤ ሙስናና ፍትሃዊነት የጎደለው አስተዳደር. . .
የፕሬዚደንት አንዋር ሳዳትን ግድያ ተከትሎ ለሰላሳ ሁለት አመታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በግብጽ ህዝብ ጀርባ ላይ በማሳረፍ የህዝቡን
ነጻነት በማሸራረፍ ለመንግስት ወታደራዊና ጸጥታ ጠባቂዎች የተሰጠው የፍለጠው ቁረጠው ህግ ለሙስናው መስፋፋት ምክንያት
እንደነበር በርካታ ምክንያቶችን እያቀረቡ መናገር ይቻላል፡፡ በዚህ ረገድ ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው በስላማዊ ሰልፍ
በአደባባይ እንዳይገልጹ፤ በእምነታቸውና በተሃድሶ ጥያቄ በማቀንቀን የግልና የቡድን ሃሳባቸውን እንዳያራምዱ የአስቸኳይ ጊዜ
አዋጁ ይደነግጋል፡፡በዚህ ህግ ከለላ የሃገሪቱ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አፈናና ግድያ በቀዳሚነት በግብጻውያን ላይ
ለደረሰው ግፍ ተጠቂ ናቸው፡፡ ዜጎች በየትኛውም ሰአት ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በጸጥታ አስከባሪዎች ተይዘው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ
ለወራትና ለአመት በድብቅ እስር ቤቶች በእስር ላይ ለመሰቃየታቸው ምክንያት ይህ ህግ ነበር፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወደ
30.000 ሰላሳ ሽህ የሚጠጉ ግብጻውያን በፖለቲካ እስረኝነት በወህኒ እንዲማቅቁ ተፈርዶባቸዋል፡፡ በሁስኒ ሙባረክ ጥርስ
ከገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የወድንማማች እስላሞች Muslim
Brotherhood የፖለቲካ ፓርቲ ላዕላይ
መሪዎች ወህኒ የከርቸመው የሙባረክ አመራር በአደባባይ ስለብዙሃን ፓርቲ እየተናገረ በስውር የሚያንሰራፋው አምባገነን
አስተዳደርን ነበር፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳቶፎ ያለበት የፖለቲካ ምህዳር እንዲጠፋ አስቸኳይ ህጉን ተመርኩዘው ትልቁን የአፈና
ሚና የተጫወቱም ሙባረክ ናቸው፡፡ በሙባረክ ገዛዝ ወፈር ያለ
የመንግስት ባለስልጣን ዝምድና አቅርቦትና ንክክኪ ያላቸው የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉባት ግብጽ ነበረች፡፡ በህገወጥ መንገድ
ከምንም ተነስተው በሙስናና በአሻጥር የአንድ ጀንበር ቢሊዮኔር ዲታ የሚኮንባት ግብጽ ምክንያቱ በሙስና የበከተው የሙባረክ
አምባገነን አገዛዝ እንደነበር የትየለሌ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ስርአት አልበኝነት ነግሷልና በነዋሪው መካከል የሃብታምና
የድሃ ልዩነቱን ክፍተት አሰፋው፡፡ በ2010 የወጣው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት Transparency International's ግብጽ በአለም ከሚገኙት 178 ሃገራት መካከል 98ኛ መሆኗን ይፋ አድርጓል፡፡
የፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ አበይት ክንውኖች በጨረፍታ. . .
በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ረገድ ፕሬዚደንት ሁስኒ ከውጭ ሃገራት ጋር ባላቸው
ግንኙነት የሃገራቸውን ጥቅም ለማስከበር የሰሯቸው ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከአረቦች ቀንደኛ ባላንጣ ከእስራኤል ጋር ያደረጓቸው
ስምምነቶች ለግብጽ ሰላም ትልቅ ሚና እንዲጫዎቱ ማድረጋቸው ይጠቀሳል፡፡ ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ በሳዳት ተጀምሮ
ያለተጠናቀቀውን ድርድር ከእስራኤል ቀጥለው ለስኬት አብቅተዋል፡፡ በሃይል የተያዘባቸውን የሲናይን ግዛት በድርድር ከእስራኤል አስመልሰዋል፡፡
በ1982 እስራኤል ሊባኖስን ወረራ ፍልጣኤማውያንን ስታጠቃ ፕሬዚደንት ሁስኒ የሊባኖስን ወረራ በመቃዎም ከእስራኤል
አምባሳደራቸውን ለጊዜው ያስወጡት ብልጣብልጡ መሪ ሁስኒ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ግን አላቋረጡም፡፡ ይህም ስምምነቱን ተከትሎ
ከአሜሪካና ከምዕራባውያን የሚፈስላቸው በቢሊዮን የሚገመት ድጎማ እንዳይቋረጥና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ረድቷቸዋል፡፡ ፕሬዚደንት
ሁስኒ በስልጡን አቀራረብ በ1988 የሰላም ስምምነት በመፈራረም በእስራኤል እጅ የነበረውን የታባ ግዛታቸውን ለግብጽ
አስመልሰዋል፡፡ ፕሬዚደት አንዋር ሳዳት ከእስራኤልን ጋር ያደረጉት ስምምነት ታላቁን የኖቤል ሽልማትና ከዚያም ለግድያ
ቢያበቃቸውም ነብሰ ገዳዮችን እያሳደዱ ስምምነቱን ሳይፈርስ እንዲቀጥል ፕሬዚደንት ሁስኒ ምክያት ነበሩ፡፡ ሳዳት ከእስራኤል ጋር
የፈረሙትን የስላም ሃሳብ የተቃወሙት አረብ ሃገራት ማህበር አረብ ሊግ አባልነት ግብጽ ከማህበርተኝነት ቢያግዳትም በአረብ ሊግ
አባልነት የታገደችው ብቸኛዋ ሃገራቸው ከስምንት አመት እገዳ በኋላ እ.ጎ.አ በ1989 እገዳው እንዲነሳ ሲያደርጉ ከካይሮ
ተነስቶ የነበረው የሊጉ ጽህፈት ቤት ተመልሶ እንዲሰየም ያደረጉት
ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ ነበሩ፡፡
የሁስኒ ሙባረክ አምባገነንነት ያመጣው የህዝብ ቁጣና ከስልጣን መውገድ !
 |
|
|
ፕሬዚደንት ሙባረክ ለሰላሳ ሁለት አመታት ከአሜሪካውያና ከምዕራባያን
ወግነውና አስዎግነው ግብጽን ሲገዙ በጎላማስነት እድሜያቸው በግብፃውያን የተቸራቸው ክብርና ዝና እየተረሳ አምባገነነነታቸው
በአደደባባይ መወገዝ ያዘ፡፡ ይህን ከ2005 ወዲህ አፈና ዘለፋ ግድያውን ተቋቁመው የቀጠሉት የወድንድማማች እስላሞች አባላትና
ደጋፊዎች አልፎ በመላ ሃገረ ግብጽ ዘንድ የፕሬዚደንት ሙባረክ መንግስት ተቀባይነት እየወረደ ሄደ፡፡ ግብጾች በሙባረክ ላይ
በተደጋጋሚ ያምጹ ገቡ ! " ክፋያ "
"በቃ" አሏቸው ! በአሌክሳንደርያ ግብጽ ከስልጣን ከመውረዳችው ስድስት ወራት በፊት በካልድ ሰኢድ
በተባለ ሰላማዊ ወጣት ላይ ወታደሮቻቸው በአሌክሳንደርያ የፈጸሙት
የግፍ ግድያ ግፉ ከአሌክሳንደርያ አልፎ መላ ግብጽን አንቀጠቀጣት ፡፡ የህዝብ ቁጣ ገንፍሎ ወጣ ! ወጣቶች በዘመነኛው
የኢንተርኔት መረብ ተደራጅተው "እኛም ነገ ካልድ ሰኢድ ነን!" ብለው በአንድ ድምጽ ፍትህን ጠየቁ ! በወርሃ
ታህሳስ መገባደጃ ከሀገር ቱኒዝ ግፍ በቃን ያለው ሙሃመድ ቡአዚዚ የአረቡን ጸደይ አብዮት ራሱን ቤንዚል አቀጣጠለ ! የተረገጡ
የተጨቆኑት አረቦች እንደ እንጉዳይ በየስርቻው ብቅ ብቅ አሉ፡፡ የቱኒዝ አመጽ ግብጽ የደረሰው ግን ከሁሉ አስቀድሞ ነበር ፡፡
እናም በፕሬዚደንት አንዋር ሳዳት ምትክ ግብጽን የመምራት በትረ ሰሎሞን በህዝብ ይሁንታ አግኝተው በክብር ስልጣን የተረከቡት
ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክ ይሁንታ በሰጣቸው ህዝብ በውርደት እንዲለቁ የተደረጉ ብቸኛ የግብጽ መሪ ሆኑ ! . . . ህዝብን
ሳያከብሩ የተጓዙት ረጅም የአንባገንነት ህይዎት "ሲያልቅ አያምር" እንዲሉ ወደ ወህኒ ወረወራቸው! በችግር ኩሩውን
መሪ ለውርደት ዳረጋቸው ! በግብጽ ሰማይ ስር የተከወነው ስር ነቀል ህዝባዊ አመጽ ለ32 አመታት ግብጽና ግብጻውያንን
አንቀጥቅጠው የገዙት ፕሬዚደት ሁስኒ ሙባረክ የአረቡ አለም የጸደይ አብዮት እንደ ቱኒዝያ፤ ሊብያና የመን መራሄ መንስግታት ሁሉ
ፕሬዚደንት ሁስኒ ሙባረክም ህዝብ በውርደት ከስልጣን አስወገዳችው
!
 |
| ሁስኒ በቃሬዛ |
ፕሬዚደት ሁስኒ ሙባረክ ፍርድ እስከረሰጣቸው ቀን ድረስ የጤናቸውን እየከፋ መምጣት ምክንያት እየሰጡ ከተደላደለው
ሆስፒታል ወጥተው ወህኒ እንዳይዎርዱ ትልቁን ሚና የተጫዎቱት ያሳደጓቸው ጀኔራሎቻቸው እነ ፊልድ ማርሻል ታንታዊ ትልቁን ሚና
ተጫውተው ተሳክቶላቸዋል፡፡ ያም ሆኖ ከፍርድና ከወህኒው ሊያድኗቸውና ሊታደጓቸው አልቻሉም ! የእድሜ ልክ እስራት ፍርድ የተሰጣቸው
ሁስኒ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ ወደ ወህኒ ተወርውረዋል፡፡ ከዚህች መራራ ቀን ወዲህ ግን የቀድሞው የሁስኒ ጤና አደጋ ላይ
መውደቁ አልቀረም፡፡ ከስልጣን የተወገዱበት አንደኛውን አመት ግብጻውያን በታህሪር የነጻነት አደባባይ በታላቅ ሃገራዊ ኩራት አክብረዋል፡፡
በወራት ልዩነትና ወህኒ በወረዱ በሁለት ሳምንታቸው ውስጥ ሁስኒ ትናንት ማምሻው ላይ የግብጽ የቁርጥ ቀኑ ልጅ ፕሬዚደንት ሁስኒ
ሙባረክ በሞት አፋፍ መትረፋቸው እውነት ነው ! . . . ያም ሆኖ ዛሬ ሙባረክ እያሉ የሌሉ ናቸው ! አያዩም ! አይሰሙም !
አይናገሩም ! የሀገረ ግብጽ የፖለቲካ ምህዳርም ቢሆን ከዚህ
ያለፈ አለሆነም !
 |
| በውርደት የተሸኙት መራሄ መንግስታት |
ግብጽ ከአንባገነን መሪዋ ነጻ በወጣች ማግስት በሃገሪቱ እየሆነ
ያለው ደስ አይልም፡፡ ሁከት ትርምሱ ግብጽን ወደ ኋላ ስላለመጎተቱና በሃገሪቱና የፈርኦንን ምድር በሌላ የፖለቲካ አዙሪት
ስላለመጣሉ ግን ዛሬ መረጃ የለም ! የግብጽ አብዮት እንደ ፕሬዚደንቱ በማጣጣር ቢያገገምም አደጋ ላይ መሆኑ መሆኑ በስፋት እየተነገረ
ያለ ተጨባጭ እውነታ ነውና ! እኔም የግብጽ የቁርጥ ቀን ልጆች በሚል ርዕስ ስር የአረቡ የጸደይ አብዮትን ተንተርሸ ስለ ግብጽ
አብዮትና ስለአራቱን የግብጽ መራሄ መንግስታትን ያዘከርኩበትን ቅኝቴን በዚህ ልቋጭ !
በቸር አስጀምሮ በቸር
ለሚያስጨርሰው አምላክ ክብር ምስጋና ይገባዋል !
ለሁሉም ቸር ያሰማን !
ቸር ይግጠመን !
አስተያየት ካለዎት በ nsirak@gmail.com መልዕክት ያድርሱኝ ! ከምስጋና ጋር
!
ሰኔ ሩፋኤል 2004 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment