በአረብ ሃገር የወገን ሰቆቃና መከራ ተጀመረ እንጅ አላበቃም !
"ልጀን እናትሽ ሞታለች ብየ አልነገርኳትም ! . . . ፈራሁ ! . .
.እንዴት አድርጌ ነው እናትሽ ሞተች ብየ የምናገረው ?" የሚለውን
የአለም ደቻሳ ባለቤት ለሜሳ እጀታን ቃለ መጠይቅ ዘጋርዲያን አውጥቶታል፡፡ ምስጋናየ ይድረሰው አንድ የፌስ ቡክ ወዳጀ Menhage Ibrahem ደግሞ ማምሻውን በኔው የፊት ለፊት ገጽ ለጥፎት አገኘሁት ! ለወዳጀን መረጃ ከአድናቆት ጋር ምስጋና እያቀረብኩ በትካዜ ፊልሙን ተመለከትኩት፡፡ አሊ ማህፉዝ የተባለው የሰራተኛ አገናኝ ደላላ ቢሮ ሰራተኛ በቤሩት ሰማይ በሃገሯ
ባንዴራና በወገኖችዋ የቅርብ ርቀት መሬት ለመሬት እያንከባለለ ሲወግራት የሚያሳየው ያ ግፍ የታየበት ፊልም የአለም ደቻሳ ባለቤት ከተካተተበት
ከዚህናው ፊልም ጋር ተቀናብሯል፡፡
በምኖርባት በምዕራባዊዋ የሳውዲዋ የወደብ ከተማ ጅዳ በረድ ብሎ የከረመው እንደ እሳት የሚፈጀው የቀን ሃሩር ሙቀት ራስ ያዞራል፡፡ ስከላተም ውየ የገባሁት አመሻሽቸ ነው ፡፡ ሰውነቴን ቀዝቃዛ ውሃ ቸፍ አድርጌበት ከመናኛዋ ፎቴ ላይ ቁጢጥ ካልኩ በኋላ ኮምፒውተሬን አስተካክየ መመልከቴ ቀጥያለሁ . . .ሳላስበው በትካዜ እጆቸን በአገጨ አስደግፊ አጭሯን ሪፖርት ሩቅ እያሰብኩ ኩርትም ብየ ተመለከትኳት፡፡
በምኖርባት በምዕራባዊዋ የሳውዲዋ የወደብ ከተማ ጅዳ በረድ ብሎ የከረመው እንደ እሳት የሚፈጀው የቀን ሃሩር ሙቀት ራስ ያዞራል፡፡ ስከላተም ውየ የገባሁት አመሻሽቸ ነው ፡፡ ሰውነቴን ቀዝቃዛ ውሃ ቸፍ አድርጌበት ከመናኛዋ ፎቴ ላይ ቁጢጥ ካልኩ በኋላ ኮምፒውተሬን አስተካክየ መመልከቴ ቀጥያለሁ . . .ሳላስበው በትካዜ እጆቸን በአገጨ አስደግፊ አጭሯን ሪፖርት ሩቅ እያሰብኩ ኩርትም ብየ ተመለከትኳት፡፡
የነፍስ ነገር . . .
ከትካዜውና ከማዘኑ አልፌ አሳሳቢ
በሆነው የአረብ ሃገር ስደተኛ እህቶች ህይወት ዙሪያ ብዙ አወጣሁ አወረድኩ ፤ አሰላሰልኩ ፡፡ ይህን የአረብ ሃገር ስደት
ለአመታት ደግሜ ደጋግሜ ስጽፍበት ሰው እንደሚያሰላች ቢገባኝም የምሰራው ነፍሴ የፈቀደውን ነውና ላፍታ ያህል ከራሴ ጋር ተጣልቸ
መልሸ ታረቅኩ ! አሁን አሁን ጥሎብኝ ያየሁ የሰማሁትን፤ ያስተምራል ፤ ያዘክራል ያልኩትን መረጃ ከራሴ ጋር ማስቀመጥ
አልፈልግም ! የተሰማኝን የውስጥ ህመሜን እንዳሻኝ ፤ የፈለግኩትን ነፍሴ የምትሻውን አደርጋለሁ ! እጽፈዋለሁ . . .
እናገረዋለሁም ! ይህ ጸባየ ከሚሰጉልኝ ከሚሳሱልኝና ነገን እንድኖር ጥሩ ጥሩውን ከሚመኙልኝ ወገኖቸ ጋር አራርቆኛል ! . .
. አሁን አሁን እየተለወጥኩ ነው ብቻ ነፍሴ ያሻትን ማድረግከ ምንም በላይ C ይሰጠኛል ! የሚያመውን የብዙሃን የተዳፈነ ሮሮ ማሰማቱ ፍትህ ያስገኘሁላቸውን
ያህል ያስደስተኛል ያረካኛል ! ይህን ማድረጌ ደግሞ ለነብሴ ዛሬን ከሚሰጠኝ እርካታ ባለፈ ከነገ ጸጸት ይሰውረኛል ! ሰላምም ይሰጠኛል ! ታዲያ ለኔ ሰላም ከሰጠኝ የመጣው ይምጣ በሚል ገፋሁበት
! እቀጥልበታለሁም . . .!
የሊቢያዋ
ሸዋየ ፤ የሊባኖስዋ አለም ደቻሳ ፤ ያልተሰሙ ያልታዩት እነ እንቶኔ እና እነ እንቶኔ . . . .
ትናንት ሸዋየ ዛሬ አለም ደቻሳ በአረብ ሃገር በኢኮኖሚ ችግር
ተሰደው መከራቸውን ለሚገፉ ወገኖችን የተደበቀ አስከፊ የሰቆቃ ህይዎት ከኛ አልፎ ለአለም ያሳዩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የሸዋየም ሆነች
የአለምን ደቻሳ ለስደት መዳረግ ዋና ምክንያት የየራሻቸው ምክንያት ቢኖራቸውም ለስደታቸው መሰረቱ ራሳቸውን ረድተው ቤተሰባቸውን
ለመደገፍ መሆኑ የማይታበል ሃቅ ስለመሆኑ የማይስማማ አለ የሚል እምነት የለኝም፡፡
ምክንያቱ ለየቅል ይሁን እንጂ እውነቱ ይህ ድህነት የኑሮ ውድነትና ችጋር ነው ! በቃ ይህው ነው ! ሰርተን
ወገኖቻቸውን ለመደገፍ የተሰደዱት ሸዋየ በሊቢያ የኮሎኔል
ጋዳፊ ቤተሰቦች የሞቀ ውሃ ላይዋ ላይ እየተቸለሰ ተደበደበችበት ፡፡ አለም ደቻሳ በሊባኖሳዊው ደላላ በሃገሯ ባንዴራና በወገኖቿ
የቅርብ ርቀር ሰቅጣጭና አስደንጋጭ ግፍ ሲፈጸምባቸው ተመለከትን ፡፡ በአረቡ አለም በሺዎች የሚቆጠሩትን የአብዛኛው የእህቶቻችንን የተደበቀ
የሰቆቃ ህይዎት በግፉአን እህቶቻችን ለአለም ገሃድ ሆነ !፡፡ ለኔና ለቀረነው ከዚህ በከፋ መንገድ እህት
ወንድሞቻችን ሰብዕናቸው ከዚህ የከፋ ሰቅጣጭ ታሪክ ሰምተን አይተናልና
ቢያንገበግበንም አይሰቀጥጠንም ! እውነቱ ይህ ነው !
ይህንኑ እውነት አስረግጦ ለማስረዳት ከሰሞኑ የሆነውን ላጫውታችሁ . . .
የአለም ደቻሳ መርዶ ከተነገረን ወዲህ ከሃገር ቤት ከመጣች ሶስት ወር ያልደፈነች እህት የ17 አመት እህት
በአሰሪዎቿ ቤት ሙታ መገኘትዋን የቤተሰቡ አባላት ገልጸውልኛል፡፡ ባሳለፍነው አርብ እዚህ ጅዳ ከተማ ውስጥ በስራ ኮንትራት ቪዛ መጥታ በስራ ላይ የነበረችው ይህችው እህት ሃሙስ ለአርብ አጥቢያ ሌሊት ለወንድሟ ስልክ በመደወል እቃ እንደሰበረችና አሰሪዎቿ
እንደተቆጧት ስትገልጽለት መጥቸ ልውሰድች ወይ ? በማለት ወንድሟ ሲጠይቃት "አንተ አትምጣ አሰሪዎቸ በጣም ስለተቆጡ ለፖሊስ
ሊያስይዙህ ይችላሉ !" በማለት እንደመለሰችለት ወንድሟ ተናግሯል፡፡ አርብ ጠዋት ግን ይህች ወጣት የለችም ! ሞታለች ! አሰሪዎቿ አርብ ከቀትር በኋላ ወደ ሟች ወንድንም ስልክ በመደወል "እህትህ ችግር ፈጠረች" ብለው ከጠሩት በኋላ ራሷን አንቃ መግደሏን በማርዳት ለወንድሟ ሬሳውን አሳይተውታል፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት በቦታው በተገኙ ፖሊሶችም የሟች ወንድምን የምርመራ ቃሉን እንዲሰጥ ካደረጉ በኋላ ልቡ በሃዘን እደተሰቀዘ ወህኒ መውረዱን የቤተሰቡ አባላት ገልጸውልኛል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ፡፡ ከሁለት ወራት በፊት እዚሁ ጅዳ ውስጥ አብሁር ተብሎ
በሚጠራው የቀይ ባህር ዳርቻ የመዝናኛ ስፍራ አንዲት እህት በተመሳሳይ ሁኔታ ሞታ ተገኝታ ግድያው በፖሊስ እየተጣራ ነው
ተባለ፡፡ ከወራት በኋላ የምርመራ ውጤቱ ይፋ ሲሆን ሟች ልትዋኝ ስትል መሞትዋን ይፋ ተደረገ ፡፡ የመንግስታችን ተወካዮች
ይህንኑ የተባሉትን ሪፖርት አስተጋቡ ፡፡ ጉዳዩን በቅርብ ይከታተሉ የነበሩትና በወቅቱ መረጃ ያቀበለኝ አንድ ወንድም ጉዳዩን
በቅርብ ያውቃሉና የሚያውቁትን ሁሉ ለቆንስል መስሪያ ቤቱ ቢያስረዱም በምርመራው የሰጡት መረጃ ግብአት አለመደረጉን እማኞች ህያው
ነን ፡፡ " . . .ይህች እህት ስትዋኝ ላለመሞትዋ መረጃዎች በሚታይበት ሁኔታ መዋኘት ስለማትችል ውሃ ውስጥ ስጥማ እንደ ሞተች ተደርጎ መነገሩ
ያሳዝናል ! " ነበር ያሉኝ
እማኝ አንጀታቸው እርር እያለ አክለውም " . . . ጉዳዩ ተዳፍኖ
የቀረው
የመንግስት ተወካዮቻችን ለጉዳዩ ምንም ትኩረት ባለመስጠታቸው ነው" ሲሉ የሰላ ሂስን በቆንስል ሃላፊዎች ላይ ሰንዝረዋል ! በዚሁ የመዝናኛ ቦታ ይህች
እህት የመሞትዋን መረጃ ለኔም ሆነ ለቆስንል መስሪያ ቤቱ በግንባር ቀርበው ዝርዝር መረጃ የሰጡት እኒሁ ወንድም የቆስንል
መስሪያ ቤቱ ይህ መሰል ወንጀል ሲፈጸም ሬሳው መመልከትና አስፈላጊም ከሆነ የፎቶና የሰው ማስረጃ በማሰባሰብ የዜጎችን መብት
ለማስጠበቅ መከራከሪያ ነጥቦችን ሳያቀርቡ የሌላውን ወገን ፍትሃዊነት የጎደለው የምርመራ ውጤት ተቀብሎ ከማስተጋባት የሚሰጡት
መረጃ መቆም እንደሚኖርበት በአጽኖት ይናገራሉ ፡፡
![]() |
| ያለ መጠለያ እስከ መቸ ? |
የዜጎች መብት ሲገፈፍ እንደማይከታተሉ የሰላ ሂስ የሚቀርብባቸው የመንግስት ተወካዮች የሩቁ ቀርቶ በአፍንጫቸው ስር ላለው ለሴት ቤት ሰራተኛ እህቶችን ችግር ግንባር ቀደም አለኝታ ሲሆኑ ማየት ናፍቆናል! በያዝነው ሳምንት በተደጋጋሚ እግር ጥሎኝ ሳይሆን ሁሌም እንደማደርገው ተፈናቃይ የኮንትራት ሰራተኞችው ወደ ሚገኙባት በጅዳ ቆንስል ግቢ ጎራ ብየ ነበር፡፡ በኮንትራት ስራ ወደ ሳውዲ መጥተው ከመጠን ባለፈ የስራ ብዛት ፤ ከውስጥ ደዌ እስከ አዕምሮን እስከመሳት በደረሰ በጤና መታወክ ፤ በደሞዝ አለመከፈል በአሰሪዎቻቸውና በቤተሰብ አባላቱ በሚደርስባቸው መደፈር ከስራ የተፈናቀሉት እህቶች ቁጥር ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ ላለፉት ሁለት ወራት አካባቢ ባለ ሁለት ዛኒጋባዋ የችግረኞች መጠለያ ፈርሳ በምትኩ ለፓስፖርት መደሻ ለቪዛ ማረጋገጫና ለመሳሰሉት ግልጋሎት መስጫ አዳራሽ ተሰርቷል፡፡ መስፋፋቱና አዳራሹ የተፈናቃይ እህቶቸን በገዛ ቤታቸው ባያፈናቅላቸው ባልጠላሁት ነበር ! ግን አልሆነም፡፡ ለሰብእና ሳይሆን ቅድሚያ ገንዘብ መሰብሰብ ሆኗልና ስራችን እህቶቻችን አዳራሽ መጠለያው ሳይቀድም አዳራሽ መቅደሙ አላስከፋኝም፡፡ ያም ሆኖ አዳራሹ ሲሰራ መጠለያቸው ለፈረሰ ወገኖች ሌላ ዛኒጋባ ቆርቆሮ መጠለያ ማሰራት ማንን ይገድላል ? ችግረኛ እህቶቻችን በቆስንስሉ ግቢና በህንጻዎች ታዛ ተወርውረዋል፡፡ ይህንን መሰል ሚዛናዊነት የጎደለው አሰራር ለመግለጽ ዛሬ ቃላት የለኝምና ልተወው !
![]() |
| እግሮችዋን የተሰበረችው እህት |
በአረቦች ምርድ ዜጎች ያለ ምንም ቅድመ ዝግጅት ከፍተኛ ቁጥር በኮንትራት ስራ
መጉረፍ ጀምረዋል፡፡ በሳውዲ አረቢያ እንደቀሩት አረብ ሃገራት በዜጎች ላይ የሚደርሰው በደል አልፎ አልፎ እንጅ ብዙም
አይስተዋልም ፡፡ ያ ግን ያለፈ ታሪክ እየሆነ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ባሳለፍነው አንድ አመት ከመቶ ሺህ የሚበልጡ የኮንትራት
ሰራተኞች መግባታቸውን በጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት ምክትል ሃላፊ ቆንስል ኑረዲን ሙስጦፋ ገልጸውልኛል፡፡ ቆንስል ኑረዲንን
በሳምንቱ መጀመሪያ ወደ ሳውዲ አረቢያ 45 000 አርባ አምስት ሽህ የሚገመቱ ዜጎቻችን ስለሚመጡበት ሁኔታና በተዛማጅ ጉዳዮች
ዙሪያ አነጋግሬያቸዋልሁ፡፡ ዝርዝር መረጃን ባደረግነው ቃለ ምልልስ ሰጥተውኛል ፡፡ ዜጎችን ለማስመጣት ሲታሰብ ስለተደረገው
የሁለትዮሽ ስምምነት ግን ጠይቅ ያሉኝ የሪያድ ሃላፊዎችን ነው፡፡ ከቆንስል ኑረዲን ሙስጦፋ ጋር ባደረግኩት ቆይታም በሃገራት
ደረጃ ስለተደረገው ስምምነት መረጃ ስለሌላቸው አልደነቀኝም፡፡ ብቻ ሙሉ ቃለ መጠይቁ ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2004 ዓ.ም በተላለፈው የጀርመን ራዲዮ ዜና መጽሄት ቀርቧል አድምጣችሁ
ፍርድን ለራሳችሁ ስጡ ! http://www.dw.de/dw/article/0,,15910204,00.html
ችግሩ አፍጥጦ መጥቷል ! መብት ጥበቃው በተደራጀ መልኩ እየተከወነ ላለመሆኑ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ተደፈርን፤ ተደበብደብን ፤ ተረገጥን እያሉ የሚመጡ ዜጎችን ችግራቸውን ሳይሰሙ ለደረሰባቸው በደል ካሳን ሳያገኙ እያንከበከቡ አፋፍነው ወደ ሃገር ቤት መላኩ ከተፈጸመባቸው በላይ ግፍ መፈጸም ይመስለኛል ፡፡ እውነቱ ቅንጭብ አድርጎ በማውጣት ፍትህን ለማምጣት የሚችል ብሩህ ልቦና ያለው ደፋር የሃገር ተወካዮች ላሉት ዜጋ የሳውዲዎች ህግ ግፍ በማንም ይፈጸም በማን ነቅነቅ አያደርግም ! ፍትህ ርትዕ ማግኘት ይቻላል ! ስለ እውነት ለመናገር እዚህ ሀገር እኛ ያጣነው የሚከራከር የሚሞግትልን የሃገር ተወካይ ዲፕሎማት ብቻ ነው ! "ልደፈር ስል ከፎቅ ላይ ወደቅኩ" ለምትለው ማስረጃ መቁጠር ቢገድ ከአሰሪዎችዋ ቤተሰብ ጽንስ ለያዘቸው ፍንትው ያለ መረጃ ማቅረብ ይቻላል ! "ባህር ገብታ ፤ ታንቃና ምንቴስ አድርጋ ሞተች ፤ ሞቱ"ለሚባለው የጣት አሸራና የረቀቀ መሳሪያ ሞልቶ በተረፈበት ሃገር እንዴት መላ መዘየድ ያቅታል ?
የሪያድ ኢንባሲ የሚቸገሩትና
የሚሳደዱት ግፉአን . . . .
በያዝነው ወር መጀመሪያ በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በመጠለያው ያየሁትን እውነት
ጉዳዩ ያሳሰባቸው ያሳዘናቸውና ያንገበገባቸው ወገኖች በኮንትራት ሰራተና እህቶቻችን ላይ እየሆነ ያለውን በኢንተርኔት
ለቀውታል፡፡ በዚህ በአየር ላይ በድህረ ገጾሽን በፊው ቡክና በዮ ቲዩብ በተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ከሶስት በላይ እህቶች
በሪያድ ኮሚኒቲ መጠለያ ኮንቴነር ውስጥ እጃቸው ታስሮ አብደው ሲጮሁ ያሳያል፡፡ ይህን መከራ በቦታው ተገኝቸ በአይኔ በብሌኑ
አይቸዋለሁ ፡፡ በፊልሙ የምትታየዋን አንዷን እህት ጨርቋን ሳትጥል በአቅሏ እያለች አነጋግሬታለሁ፡፡ በቀናት ልዩነት ግን
ይህንን የተለቀቀ ቪዲዮ ስመለከት አብዳና የፍጥኝ ታስራ ስመለከት ቅስሜ ተሰበረ ፡፡ በእርግጥ ይህን መሰሉን ደረቅ እውነት አሰቃቂ
ገጽታ ሲናገሩትና ሲጽፉት የስቃዩን አስከፊነት ምሉዕ አድርጎ መግለጽ አይቻልም፡፡ በመጠለያው ካበዱት በከፋ ሁኔታ በአብዛኛው
በአገድዶ መድፈር በጠና የታመሙ የሚገኙበት ሲሆን የማይሰሙ የማይናገሩትም ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡ የምክር አገልግሎት ያግኙ
ማለትም የቅብጠት ሊሆን ይችላል፡፡ ካበዱት ጋር ውለው የሚያድሩት የቀሩህ በተመሳሳይ የዓዕምሮ ህመም ሊዳረጉ ነው ብሎ ሌላ
መጠለያ ይፈለግል ማለትም ድሎት መፈለግ ሊሆን ይችላል፡፡ጠበሳቸውን እያሳዩ ጉዳታቸውን እያስረገጡ ፍትህን ርትዕ እንዲያገኙ
መጠየቅ የሃገራችን ገጽታ የሃገራቱን መልካም ግንኙነት ያበላሻል ተብሎ ይዳፈን፡፡ እንዴት የሃገር ተወካዮች ባሉበት በህዝብ ስም
የተመረጡ የማህበረሰቡ ተወካዮች በተሰበሰበው ገንዘብ ተቆጣጣሪ አጥተው በሙስና በሚናኙበት ሃገር በመናኛ መጠለያ ለተጣሉ ወገኖች
ስቃይ እንዲህ መረን ለቆ ማየት ያሳዝናል፡፡ ለተቸገሩት የእለት ጉርስና ቀዝቃዛ ውሃ በአግባቡ እንዲያገኙ መጠየቅ፤ አለያም ወደ
ሃገራቸው የሚሄዱበትን መንገድ እንዲመቻች ወደ መንግስት አቤት ማለት የድሎትም የቅብጠትም የተቃውሞም ሆነ የማሸበር ጥያቄ ሊሆን
አይገባውም፡፡ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንዲሉ በያዝነው ሳምንት ወደ ሪያድ ብቅ ብየ በነበረበት አጋጣሚ ተንቀሳቃሽ ፊልሙን
ቀረጹ የተባሉ ሰወች በኢንባሲው ታደነው ለጥያቄ ከቀረቡ በኋላ ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸውን እስከመቀማት የደረሰ እርምጃ መወሰዱን
ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ የማጣራሩ ጉዳይ ሃገር ቤት ድረስ በመጡ የውጭ ጉዳይና የደህንነት አባላት እየተካሄደ ስለመሆኑ ማረጋገጫ
ባይኖርም ምርመራው ስለመካሄዱ በእርግጠኝነት ለመናገር የሚያስችሉ መረጃወች አሉኝ፡፡ ግን ለምን ? ነው ጥያቄው . . . እኒህ
መርማሪዎች መመርመር ያለባቸው ያበዱና በሰቆቃ ላይ ያሉ እህቶችን በደል መሆን ሲገባው በደሉን መፍትሄ ሲያጣ "የሰው
ያለህ!" ብለው በተቆርቋሪነት ስሜት የተቻላቸውን ሁሉ ያደረጉትን ቅን ዜጎች መሆን አልነበረበትም፡፡ መታደን ያለባቸው
በዜጎች ላይ በደል ሲፈጸም መብቱን ማስጠበቅ ያለቻሉትን ሃላፊዎች እንጂ እውነቱን ገሃድ ያወጡትን አልነበረም፡፡ የሚያሳዝነው ትናንትም
ዛሬ እየሆነ ያለው የተገላቢጦሽ ነው !
በእርግጥ በአረብ ሃገር የሚደርሰው የወገን ሰቆቃና መከራ የምንሰማበት የታሪክ
ምዕራፍ ተጀመረ እንጅ አላበቃም ! ያለመታደል ሆኖ ችግር መከራው ሲበዛ ኑሯችን ሊከብድ ነው ! መረጃ
ቅበላውም ቢሆን እየከበደ መጥቷል ፡፡ በሃገሬው በነጻነት የሚንቀሳቀሱት ሚዲይወች ውስን ናቸው ! የአሜሪካ የአሜርካን መንግስት
አቋም ያስተናግዳል ! የጀርመንም እንደዛው ! አንዳንዴ ፈረንጆች ሳይቀር አፈና ይወዳሉ እኮ ! በነጻነት በተለያዩ ድህረ ገጾ
መጻፍ መረጃን ላልሰሜው ማቀበል በአደባባይ በፍርድ ቤት ባያስቀጣም እያሰለሰም ቢሆን በአንዳንድ ወገኖቸ የሚሰነዘረው ጉሸማ
አልተለየውም ! የምናውቀውን ለማሳዎቅ የዜግነት ግዴታችን እንዳንዎጣ ጋሬጣው በዝቷል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ መረጃን መቀባበል
የሚቻልበት ቦታ እንዳይጠፋ እየሰጋሁ ነው ! እውነት እላችኋለሁ ይህችን የማለዳ ወጌን ግን የሚያስቆመኝ የለም !
ቸር ያውለን ! ቸር ያሰማን !



No comments:
Post a Comment